አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 6 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም በ2013 ዓ.ም የደንበኞቹ ቁጥር 56 ነጥብ 2 ሚሊየን መድረሱን ገለጸ።
ኢትዮ ቴሌኮም የ2013 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀሙን ሪፖርት እያቀረበ ይገኛል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ በሪፖርቱ እንደገለጹት፥ የደንበኞች ቁጥር በበጀት ዓመቱ ከተያዘው እቅድ108 በመቶ ማሳካት ተችሏል።
ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸርም 22 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
በተጨማሪም በ2013 በጀት ዓመት 56 ነጥብ 5 ቢለየን ብር ገቢ የተገኘ ሲሆን፥ በዚህም የእቅዱን 101 ነጥብ 7 በመቶ ማሳካት መቻሉ ተገልጿል።
በበጀት ዓመቱ 70 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ክፍያ የፈጸመ ሲሆን÷ ከዚህ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት 26 ነጥብ 6 ቢሊየን ብሩ ለግብር ክፍያ እና 29 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ደግሞ ለተለያዩ የማስፋፊያ ስራዎች የተከፈለ መሆኑ ተመላክቷል።
በ2018 በወር የሚያገኘው የውጭ ምንዛሬ 5 ነጥብ 98 ሚሊየን ዶላር የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ወደ 14 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር
ማሳደግ ተችሏልም ነው የተባለው።
የቴል ብር ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር 6 ነጥብ 5 ሚሊየን ደርሷል።
ተቋሙ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣትም ለተለያዩ ፕሮጀክቶች 847 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል።
በዓመቱ ለ103 ከተሞች የ4ጂ እን የ4ጂ አድቫንስድ አገልግሎት ለማስጀመር ታቅዶ ለ68 ከተሞች ማዳረስ ተችሏል። በተቀሩት ከተሞች ላይም በቀጣይ የማስጀመር ስራዎች ይሰራሉ ተብሏል።
የበጀት ዓመቱን ስኬት ምክንያት በማድረግም ለደንበኞች ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀን የሚቆይ የ303 ፍሌክሲ ዩኒት እና የ1 ጂቢ ኢንተርኔት አገልግሎት በነጻ ተሰጥቷል። አገልግሎቱ ከ ለሊት 6ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት የሚሰራ ነው።
በዘመን በየነ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

