አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር የኮቪድ 19 ክትባትን በስፋት ለማዳረስ እየሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፥ ከ2 ሚሊየን በላይ ዜጎች የመጀመሪያ ዙር ክትባት መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡
ከ42 ሺህ በላይ ዜጎችም የ2ኛው ዙር የኮቪድ19 ክትባት መውሰዳቸውን ነው የገለጹት፡፡
ክትባቱ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በተከሰተ እጥረት መዘግየቱን ያነሱት ዶክተር ሊያ፥ በቅርቡ 400 ሺህ የሚጠጋ የአስትራዜኒካ ክትባት ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን አስታውሰዋል፡፡
በዚህም ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከአርብ ጀምሮ ደግሞ በክልሎች የመጀመሪያውን ክትባት ከወሰዱ 3 ወር የሞላቸው ዜጎች ክትባቱን መውሰድ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
ተጨማሪ ክትባቶችን የማፈላለግ ስራ እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስት፥ በዚህኛው ዙር ክትባት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዜጎች ዝርዝርም ይፋ አድርገዋል፡፡
በዚህ መሰረትም የትራንስፖርት ዘርፍ ሰራተኞች( የአውቶብስ እና የሚኒባስ ሹፌሮች)፣ የመንግስትና የግል ባንኮች ሰራተኞች፣ የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ቢሮዎች ሰራተኞች፣የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና የማረሚያ ቤቶችና የፍርድ ቤቶች ሰራተኞች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡
በተጨማሪም የውልና ማስረጃ እንዲሁም የማዘጋጃ ቤት ሰራተኞች፣መምህራን የህጻናት ማቆያ የመደበኛና የኮሌጅ መምህራን፣የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ሰራተኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች ቅድሚያ የሚሰጣቸው መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የመጀመሪያ ዙር ክትባት የሚወስዱ ዜጎች ሁለተኛው ዙር ክትባት ከ3 እስከ 4 ሳምንት ስለሚሰጥ ዜጎች ክትባቱን እንዲወስዱም የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታውሰዋል።
የኮቪድ- 19 ምርመራን በተመለከተም በ20 ደቂቃ የሚያደርስ ፈጣን ምርመራ ማድረጊያ መሳሪያ ለክልሎች መሰራጨቱን ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ አልፋ እና ቤታ የተሰኙ የቫይረሱ ዝርያዎች መኖራቸው የተረጋገጠ ሲሆን÷ የዴልታ ዝርያ ስለመኖሩ ለማረጋገጥ ስራዎች መጀመራቸውም ተነስቷል።
በምስክር ስናፍቅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

