አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ለ2014 በጀት ዓመት 124 ቢሊየን ብር ረቂቅ በጀት ማዘጋጀቱን ገልጿል።
የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ሀምሌ 9 እና 10 ቀን የሚካሄደውን የጨፌውን መደበኛ ጉባኤ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
ምክር ቤቱ በ14 መደበኛ፣ 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 6ኛ ዓመት ጉባኤው የ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀት ማጽደቅን ጨምሮ 11 አጀንዳዎች ላይ ውይይት ያደርጋል ተብሏል።
አፈ ጉባኤዋ በመግለጫቸው በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት በአብዛኛው ለካፒታል ስራ የዋለ የ14 ቢሊየን ብር ተጨማሪ ረቂቅ በጀት ይጸድቃል ብለዋል።
ኦሮሚያ ክልል በዚህ ዓመት ከ11 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ ከፍተኛ ወጪ ማውጣቱና በዋጋ ግሽበቱ ምክንያት ተጨማሪ በጀት ማስፈለጉን ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም የመንግስት የተለያዩ ዘርፎች እቅድ ክንውን የሚቀርብ ሲሆን፥ የቀጣይ ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይም ውይይት ይደረጋል ነው ያሉት።
ከአዋጆች አንጻርም ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ጎን ለጎን እንዲሰሩ የሚያስችል አዋጅ እንደሚጸድቅ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በጀቱ በተመሳሳይ ክልሉ ለሚያከናውናቸው የካፒታል ስራዎች እንደሚውልም ነው አፈ ጉባኤዋ የገለጹት።
ጨፌ ኦሮሚያ በ2013 በጀት ዓመት 10 አዋጆችንና 5 ደንቦችን አጽድቆ የህዝቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉንም አስታውሰዋል።
የክልሉ ምክር ቤት አባላት በምርጫ ዙሪያ፣ በኮቪድ19 እና በሕብረተሰብ ተሳትፎ የሚሰሩ ስራዎች ላይ ብዙ መልካም ነገሮችን ማከናወኑንም ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በነገው እለት ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ 3 ሺህ ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀታቸው ተገልጿል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

