Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለ2013/14 የመኸር ወቅት እስካሁን 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል – የግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 8፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ለ2013/14 የመኸር ወቅት እስካሁን 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ገልጸዋል።

በመኸር ወቅቱ በተለያዩ ሰብሎች ይሸፈናል ከተባለው 13 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብሎች መሸፈኑን ሚኒስትሩ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት 6 ሚሊየን ሄክታሩ በዘር መሸፈን እንደነበረበትም ገልጸዋል።

ወቅቱን ውጤታማ ለማድረግ ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ የባለሙያ እና መሰል አስፈላጊ ግብዓቶችን የማዘጋጀት ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት ሚኒስትሩ፥ ሆኖም ከዝናብ እጥረት እና መሰል ምክንያቶች ጋር በተያያዘ የተያዘውን እቅድ ማሳካት ባይቻልም የዘር መዝራት ስራው በጥሩ ሁኔታ እየተከወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ ዓመት ለወቅቱ ይቀርባል ከተባለው 18 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ 92 በመቶ ያህሉ መግባቱንም ነው የተናገሩት።

እንደ አጠቃላይ ጥሩ የማዳበሪያ አቅርቦት እንዳለ የተናገሩት አቶ ዑመር፥ ከዓለም አቀፍ የገበያ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ እጥረት የታየበት የዩሪያ ማዳበሪያ አይነት ይቀርባል ከተባለው ውስጥ 72 በመቶ መግባቱን እና ቀሪው እየተጓጓዘ መሆኑን አስረድተዋል።

ምርጥ ዘር ላይ ያሉ እጥረቶችን ለዚህኛው ወቅት ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ለመፍታት ከክልሎች ጋር የዘር ማባዛት ስራዎች በስፋት እንዲሰሩ እየተደረገ ነውም ብለዋል ሚኒስትሩ።

አረምና መሰል ምርታማነትን ሊቀንሱ የሚችሉ የሰብል ተባዮችን መከላከል የሚያስችሉ ኬሚካሎችን ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ከውጭ የማስገባት እና በሀገር ውስጥ የማምረት ስራዎችም እየተከወኑ ነው ተብሏል።

በቡድን እና በግለሰብ ደረጃ ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ ለማድረግ ሰፊ ዝግጅት ተደርጓልም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

ሰፊ ምርት በሚጠበቅበት መኸር ‘‘አንድም መሬት ፆም ማደር የለበትም’’ የሚለውን ዘመቻ ውጤታማ ለማድረግ በዚህ የመኸር ወቅት 300 ሺህ ሄክታር ተጨማሪ መሬት ታርሷል ብለዋል።

ከ2013/14 የመኸር ወቅትም 375 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

በዙፋን ካሳሁን

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version