Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የህወሓት ርዝራዦችና ደጋፊዎች ኢትዮጵያን ለማዋረድ የሚያደርጉትን ፍትጊያ ለመቀልበስ ተነሳስተናል – አቶ ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 8 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሸባሪው ህወሓት ርዝራዦችና ደጋፊዎች በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያን ለማዋረድና ሠላሟን ለማናጋት የሚያደርጉትን ጥረት ለመቀልበስና ለመመከት ተነሳስተናል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ለተሰናዳው ለሲዳማ ክልል ልዩ ሀይል አባላት ትናንት ማምሻውን በሀዋሳ ከተማ የሽኝት ስነ ስርአት ተካሂዷል።

በስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንዳሉት ህወሓት ዜጎች በተባበረ ክንድ ከስልጣን ቢያስወግዱትም ተመልሶ ለመምጣት በሚያደርገው ጥረት ሀገሪቱን እየተፈታተናት ይገኛል።

“አሸባሪ ኃይሉ የመንግስትን የተኩስ አቁም ውሳኔ ውድቅ በማድረግ በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት በማያዳግም ሁኔታ ማስቆም ያስፈልጋል” ብለዋል።

“በተለይ ቡድኑ የኢትዮጵያን ከፍታ ከማይወዱና ሀብቷን በእጅ አዙር ከሚጠቀሙ ከጎረቤትና ኃያላን ሀገራት ጋር በመተባበር እያደረሰ ያለውን ፈተናና መዳፈር ሁሉም ዜጋ በቁጭትና በጋራ ለመቀልበስና ለመመከት ልንነሳሳ ይገባልም” ነው ያሉት።

በተለይ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በጋራ በመመከት አንድነትን በማፅናት የህዝቡን ክብር ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

“የሀገሪቱን ዳር ድንበር ለማስጠበቅና ለማስከበር የሲዳማ ልዩ ሃይል ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በመሰለፍ ቁርጠኛ አቋምና ወኔ በመሰነቅ ተነሳስቷል” ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

ርእሰ መስተዳድሩ ለልዩ ሀይሉ ባስተላለፉት መልእክት “የጥንት አባቶቻችንን ፈለግ በመከተል በፍጹም ጀግንነትና በልበ ሙሉነት በድል እንደምትመለሱ በመተማመን በክብር ሸኝተናችኋል” ብለዋል።

“የክልሉ መንግስትና ህዝብ ከጎናቸው ይሆናል” ሲሉም አረጋግጠዋል።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በበኩላቸው የክልሉ ልዩ ኃይል ወቅቱ ለሚፈልገው ሀገራዊ ተልዕኮ ግዳጁን ለመወጣት ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልፀዋል።

ለግዳጅ የተሰማራው ልዩ ኃይል አስተባባሪ ዋና ኢንስፔክተር ቦጋለ ገላልቻ ልዩ ኃይሉ ተልዕኮውን ለመወጣት ከእነ ሙሉ ትጥቁ ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ ግዳጁንም በስነ ምግባር፣ በደስታና በሞራል ለመፈጸም ዝግጅት አድርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version