አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በባህሬን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በክር ከባህሬን የስራ ገበያ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ዋና ስራ አስፈጻሚ ጀማል አል አላዊ ጋር በበይነ-መረብ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በወቅቱም አምባሳደር ጀማል በክር ከዚህ ቀደም ሁለቱ ሃገራት የተለዋወጡትን የውጭ ሃገር የስራ ስምሪት ሪቂቅ መግባቢያ ሰነድ በአፋጣኝ ወደ ፊርማ ስለሚሸጋገርበት ሁኔታ አንስተዋል።
አያይዘውም በባህሬን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መብትና ደህንነት ተጠብቆ ስለሚሰሩበት፣ አልፎ አልፎ በአሰሪዎቻቸው የደመወዝ ክልካላና የመብት ጥሰቶች የሚደርስባቸው ዜጎች መብታቸው እንዲጠበቅ እንዲሁም ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ለመቀነስ ህጋዊ የስራ ስምሪት በማፋጠን የሁለቱን ሃገራት የኢኮኖሚና የማህበራዊ ትስስር የሚጠነክርበት ጉዳዮችን አንስተዋል ፡፡
በተጨማሪም አምባሳደሩ በተለያያ ምክንያት በባህሬን ህጋዊ የስራና የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን የባህሬን መንግስት ምህርት እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።
የባህሬን የስራ ገበያ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ዋና ስራ አስፈጻሚ ጀማል አል አላዊ በበኩላቸው÷ ሁለቱ ሃገራት የተለዋወጡት ረቂቅ የውጭ ሃገር ስራ ስምሪት መግባቢያ ሰነድ ወደ ፊርማ እንዲሸጋገር ለማድረግ መስሪያ ቤታቸው ከሰራተኛና ማህበራዊ ልማት ሚኒስቴር ጋር እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው በቅርቡ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አያይዘውም ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቀነስና ለመከላከል በቅርበት ከሚሲዮኑ ጋር በጋራና በትብብር ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
በተጨማሪም ያለ ህጋዊ የስራና የመኖሪያ ፈቃድ በባህሬን የሚኖሩ ዜጎች የምህረት ጥያቄ በተመለከተ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ምላሽ እንደሚሰጥበት አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በአሰሪዎቻቸው የደመወዝ ክልካላንና ተያያዥ የመብት ጥሰት የሚደርስባቸው ዜጎች የመብት ጥሰት በተመለከተ ተቋማቸው በቅርበት ከቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ጋራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
በመጨረሻም ሁለቱ ኃላፊዎች የሁለቱ ሀገራትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር በትብብር ለመስራት መግባባት ላይ መድረሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

