Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሊባኖስ ዜጎች ችግር ሲገጥማቸው ድጋፎችን ላደረጉ አካላት የምስጋና እና የዕውቅና መርሃ ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 12፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በሊባኖስ ዜጎች ችግር ሲገጥማቸው ድጋፎችን ላደረጉ አካላት የምስጋና እና የዕውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር ተካሄዷል፡፡
መርሃግብሩን የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄነራል ጽህፈት ቤት ከኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ማህበር ጋር በመተባበር አዘጋጅቷል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፅዮን ተክሉ በመርሃ ግብሩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ በሊባኖስ በተከሰተው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ ብዙ ዜጎች የተለያዩ ችግሮች ሲደርሱባቸው መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

ሆኖም በሊባኖስ በሚገኙ የተለያዩ ማህበራትና ግለሰቦች ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ አለም አቀፍ ድርጅቶች ከቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ጋር በቅንጅት በመሰራታቸው ሁሉም መስመር መያዙን አንስተዋል፡፡

ሁሉም አካላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ማመስገናቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በሊባኖስ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቆንስል ጄኔራል አቶ ተመስገን ዑመር በበኩላቸው፥ የኮሚዩኒቲ ማህበሩ ዜጎችን ለመርዳት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል፡፡

አክለውም በዚህ ዓመት ብቻ ከ6ሺህ በላይ ሰነድ አልባ ዜጎችን ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ትኬት በማቅረብና የተለያዩ አስተዋጽኦ ላደረጉ የሃይማኖት ተቋማት፣መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ፣ማህበራትንና ግለሰቦችን አመስግነዋል፡፡

የኮሚዩኒቲ ማህበሩ ሊቀመንበር ዲያቆን በኃይሉ ጌታነህ በበኩላቸው፥ በአሁኑ ወቅት በሊባኖስ ባለው የኢኮኖሚ ቀውስ ብዙ ዜጎች ለእንግልት እየተዳረጉ መሆኑን ጠቅሰው፥ የማህበሩ አባል ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን የማህበሩ አባል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ጎን በመሆን ለዜጎቸ የአውሮፕላን የትኬት ወጭ፣የአልባስት፣የንጽህና መጠበቂያ አንዲሁም የተለያየ አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦች፣ማህበራት፣የሃይማኖት ተቋማት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የምስጋና የምስክር ወረቅት ተሰጥቷል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version