Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በጣና ሀይቅ በተሰወረችው ጀልባ ህይወታቸው ያለፈ የ7 ሰዎች አስከሬን ተገኘ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 12፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በማእከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ በጣና ሀይቅ 13 ሰዎችን አሳፍራ በጉዞ ላይ እንዳለች በተሰወረችው አነስተኛ ጀልባ ህይወታቸው ያለፈ የሰባት ሰዎች አስከሬን መገኘቱን ፖሊስ አስታወቀ።
የወረዳው ፖሊስ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ምክትል ኮማንደር ቸርነት አስማረ እንደገለጹት አስከሬኑ የተገኘው በሃይቁ ላይ ላለፉት ሁለት ቀናት በጀልባና በዋናተኞች በተካሄደ አድካሚ ፍለጋ ነው፡፡
አስከሬኑ የጣና ሀይቅ በሚያዋስናቸው በጎርጎራና አዲስጌ ድንጌ በተባለ የገጠር ቀበሌ መካከል በሀይቁ ላይ በማእበል ተገፍተው ዛሬ ንጋት ላይ ተንሳፈው መገኘቱን አስረድተዋል፡፡
የቀሪውን የስድስት ሰዎች አስከሬን ለማግኘት ፍለጋው ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው የጀልባዋን መስመጥ የሚያጣራ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ምርመራ መጀመሩን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ጀልባዋ ሐምሌ 9 ቀን 2013 ዓም ሌሊት ድንች የጫኑ 13 ሰዎችን አሳፍራ በወረዳው አዲሰጌ ድንጌ ተብሎ ከሚጠራ ቀበሌ አባን ላይ ጎጥ መነሻዋን በማድረግ ወደ ጎርጎራ ወደብ በጉዞ ላይ እንዳለች መሰወሯ ይታወሳል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
.
Exit mobile version