አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 12፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) “የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የኢትዮጵያዊያን ልዩ የድል ብስራት ቀን ነው” ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ የግድቡ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
የግድቡ ውሃ ሙሌት አሁን ያለብት ደረጃ እንዲደርስ ኢትዮጵያዊያን በከፍተኛ ቁርጠኝነትና ትብብር ሰርተዋል ያሉት ጀነራል ብርሃኑ፤ ግድቡ የሞላበት የዛሬው እለት “የኢትዮጵያዊያን ልዩ የድል ብስራት ቀን ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ማንንም አገር የመጉዳት ፍላጎትና ዓላማ እንደሌላት ገልጸው፤ የግድቡ የውሃ ሙሌትም ይህንን በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ አክለቅውም የሕወሃት አሸባሪ ቡድን መንግስት ለትግራይ ሕዝብ የሰጠውን የጥሞና ጊዜ በመጠቀም ትንኮሳዎችን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አሸባሪ ቡድኑ ለትግራይ ህዝብ ደንታ ቢስ መሆኑና ህዝቡን ለከፋ ችግር ለመዳረግ ቆርጦ መነሳቱን አመላካች ስለመሆኑም ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።
የአገር መከላከያ ሰራዊት ከመቸውም ጊዜ በላቀ መልኩ በጠንካራ ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ።
በመሆኑም አሸባሪ ቡድኑ ትንኮሳዎችን የሚቀጥል ከሆነ ሰራዊቱ በሚሰጠው ትዕዛዝ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነው ሲሉ አረጋግጠዋል።
የትግራይ ህዝብም በተሰጠው የጥሞና ጊዜ በመጠቀም አሸባሪውን የህወሃት ቡድን “ሊዋጋውና በቃህ ሊለው ይገባል” ብለዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

