አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የታላቁ የሕዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር ውኃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ በመጠናቀቁ የተሰማውን ልባዊ ደስታ ገለጸ፡፡
ምክር ቤቱ ደስታውን በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለወዳጅ ሀገራት እና ግለሰቦች ሁሉ በታላቅ ኩራት እና ሀገራዊ ስሜት በድጋሚ ያበስራል ነው ያለው በመግለጫው፡፡
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የአንድነታችን ማኅተም፣ የለውጥ ጉዟችን አውታር እንዲሁም የላባችን እና የጥረታችን ማሳያ እንደሆነ ከእኛ አልፎ መላው ዓለም ተረድቶታልም ብሏል፡፡
ይህም በቅርቡ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ባሰማነው የፍትሐዊነት ሐሳብ፤ ዓላማችን በጋራ ሀብት የዕኩል ተጠቃሚነት መርህ መከተል መሆኑን በማያወላዳ አኳኋን ለሚመለከታቸው ሁሉ አስገንዝበናል ነው ያለው ምክር ቤቱ፡፡
ይህ የጀመርነው የልማት ጉዞ በሁሉም ዘርፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪውን አቅርቧል፡፡
“በተለይም በአሁኑ ወቅት የውስጥ እና የውጭ ጠላቶቻችን ባለ በሌለ ዓቅማቸው ሀገራችንን ለማፈራረስ እየሠሩ ባሉበት ሁኔታ፤ የእኛ አንድ ሆኖ መቆም ምርጫ የሌለው አማራጭ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል” ብሏል፡፡
ይህንንም በጽኑ ዕምነት አጠናክረን የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅብናልም ነው ያለው፡፡
በሌላ በኩል የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመላው የእስልምና ሐይማኖት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 442ኛው ዓመተ-ሒጅራ የዒድ አል-አድሐ ዐረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ሲልም መልዕክቱን እተላልፏል፡፡
በዓሉ በሚገርም ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ ከ2ኛው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት ጋር መጣጣሙ ደግሞ ልዩ አድርጎታል፡፡
ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ ያበረከተውን ወደር-የለሽ አስተዋጽዖ ታሪክ መቼም አይረሳውምም ነው ያለው ምክር ቤቱ፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

