አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 13 ፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ አኒት ዌበርን ጋር ተወያዩ ።
አቶ ደመቀ በውይይታቸው የ6ኛውብሔራዊ ምርጫ እጅግ ሠላማዊ ሆኖ በስኬት መጠናቀቁን ገልፀዋል።
ህወሓት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ መንግሥት ህግ የማስከበር ዘመቻ ማድረጉ የጠቆሙት አቶ ደመቀ፣ የህግ ማስከበር ዘመቻው በአጭር ጊዜ የተጠናቀቀ ቢሆንም በህግ የሚፈለጉ የጥቃቱ አቀናባሪዎችን ለህግ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት በመራዘሙ ህወሓት ህዝንቡን እንደ ሰብአዊ ጋሻ መጠቀሙን ገልጸዋል።
በዚህም ህፃናት፣ አዛውንቶችና አርሶ አደሮችን ወደ ማሰለፍ በመግባቱ መንግሥት በክልሉ ያለውን የሰብአዊ አቅርቦቶች ሁኔታ እንዲሻሻል እንዲሁም በክረምቱ ወቅት ህዝቡ ተረጋግቶ የእርሻ ሥራዉን እንዲያከናውን የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ማስተላለፉን ገልፀው÷ ነገር ግን የጁንታው ኃይል ውጊያ መቀጠሉን አስረድተዋል።
የሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዲደርስ በመንግሥት በኩል ሁኔታዎችን የማመቻቸት ጥረት መቀጠሉን፣ በዚህም የመጀመሪያ ዙር እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መቀሌ የደረሱ መሆኑን እና የሁለተኛ ዙርም ወደ ክልሉ በመጓጓዝ ላይ እንዳለ በህወሓት ጥቃት እንደተፈፀመበት ጠቅሰዋል።
አቶ ደመቀ የህወሃት ቡድን ግጭትን የሙጥኝ ብሎ መቀጠሉንና ህፃናትን ሳይቀር በውጊያ እያሳተፈ መሆኑን ጠቅሰው፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ህወሃትን እንደተጠቂ ከመቁጠር ወጥቶ በሚያደርገው የጦርነት ማስቀጠልና ህፃናትን ለጦርነት የማሰለፍ ድርጊቱን እንዲያወግዝ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም በትግራይ ተፈፀሙ የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አስመልከቶ መንግሥት ቃል በገባው መሰረት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ተቋም ጋር የጋራ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን፣ የጠቅላይ አቃቤ-ህግና የፌዴራል ፖሊስ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ አካላትን በመለየት ተጠያቂ የሚያደርጉበት ሁኔታ ያለ መሆኑ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከአፍሪካ ህብረት የሰብአዊ መብትና የህዝቦች መብት ምክር ቤት ጋር በጋራ ምርመራ እንዲያደርጉ ቃል የተገባው ሂደቶች በመከተል ተጠያቂነት ለማስፈን እየተሰራ መሆኑንም አብራርተውላቸዋል።
የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ላይ በተ.መ.ድ የሰብአዊ መብት ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ እንዲወጣ ማድረጉ የተቻኮለ፥ የኢትዮጵያ መንግሥት እያደረገ ያለውን ተጨባጭ ጥረት ያላገናዘበና ኢትዮጵያን ያሳዘነ ድርጊት መሆኑንም ገልፀውላቸዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተም የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኃይል አቅርቦት እጥረት ምክንያት በጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ከስልሳ ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ኑሮ ለማሻሻል የሚገነባ የልማት ፕሮጄክት መሆኑን አስታውሰው÷ በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚካሄደው ሂደት እንዲቀጥል ኢትዮጰያ ቁርጠኛ ብትሆንም በሱዳንና ግብጽ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ም/ቤት በመወሰድ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲላበስ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም የፀጥታው ምክር ቤትም ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ህብረት የመለሰው መሆኑንም ገልፀውላቸዋል ።
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በዚህ ዓመት የተያዘው የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ የተከናወነ መሆኑን የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የዘንድሮ የክረምቱ ዝናብ ከመደበኛ በላይ በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለታችኛቹ የተፋሰሱ አገራት የሚጠቅም እንጂ ጉዳት እንደማያደርስ ገልፀዋል።
አያይዘውም የአውሮፓ ህብረት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት መካሄድ እንደሚያሳስበው በህብረቱ የተለያዩ ኃላፊዎች መገለፁ፣ ተገቢ ያልሆነ እና ኢትዮጵያን ያሳዘነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ አስመልክቶም የኢትዮጵያ አቋም ሁለቱ አገራት ቀደም ሲል በድንበር ጉዳይ በዘረጉት የጋራ አሰራር መሰረት ችግሩ እልባት ሊያገኝ እንደሚችል ጠቁመው፣ ነገር ግን ሱዳን በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ በኃይል ለመቀየር ያደረገችውን ኢትዮጵያ የማትቀበል መሆኑን አንስተዋል።
የአውሮፓ ህብረት ልዩ ተወካይ አኒት ዌበር በበኩላቸው ለተደረገላቸው ገለፃ አመስግነው÷ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር ተገናኝቶ የተጀመሩ ምርመራዎች በፍጥነት ተገባደው ይፋ የሚደረጉበት ሁኔታ እንዲፋጠን የአውሮፓ ህብረት እንደሚፈልግ ጠቁመዋል።
አክለውም በትግራይ ክልል የከፋ የሰብአዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው መሆኑንና ይህ እንዳይፈጠር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
በመጨረሻም አቶ ደመቀ የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ ያለችበት የምስራቅ አፍሪካ ያልተረጋጋና አስቸጋሪ ቀጠና መሆኑን በመረዳት በኢትዮጵያ ላይ አላስፈላጊ ጫና ከማድረግ ይልቅ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ማድረግ በሚችልበት ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

+2
0
People Reached
0
Engagements
Boost Post
Like
Comment
Share

