አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ዳር ድንበር እያስከበረ የሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የህዝብ ደጀን እንደመሆኑ ህዝቡም ደጀኑ ሊሆንለት ይገባል ተባለ።
በወላይታ ዞን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የድጋፍ እና በሁለተኛው ዙር የሕዳሴ ግድብ ሙሌት የተሰማቸውን ደስታ በሰልፍ ገልጸዋል።
በሰልፉ ከሁሉም ወረዳዎችና ከተማ መስተዳድሮች የተሰባሰቡ ነዋሪዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ደስታቸውን ገልጸዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እንድሪያስ ጌታ ለሰልፈኞቹ ምስጋና አቅርበው “እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቆርጠን በመነሳት ታሪክ መስራት እንደምንችል ያስመሠከርንበትና ከአድዋ በመቀጠል የዚህ ትውልድ ሁነኛ ገድል የሆነው ታላቁ ህዳሴ ግድብ ከሀገራችን አልፎ ለመላው አፍሪካውያን የይቻላል መንፈስን ዳግም ያሳበበ መነሳሻ ነው” ብለዋል።
የዞኑ ሕዝብ የሀገሪቱ ሰላምና እድገት ባለድርሻ እንደመሆኑ የአማጽያኑን ሴራ ለማክሸፍ ሙሉ ቁርጠኝነት ያለውና በየትኛውም ጊዜ ከሀገር መከላከያ ጎን የሚሰለፍ መሆኑን ተናግረዋል።
ሰልፈኞቹ የጦር መሳሪያ ከትግራይ ህፃናት ትከሻ ይውረድ የሚል መፈክር አሰምተዋል።
እስክሪብቶና ደብተር ይዘው ቀለም በመቁጠሪያቸው አመት ጨካኙ ሕወሐት የጦር መሳሪያ አሸክሞ ማሰለፉ ወትሮም ለትውልድ ደንታ የሌለውና የሀገር ተረካቢ ዜጋ አምካኝ መሆኑን እንደሚያምኑም ሰልፈኞቹ ገልጸዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር ሙሌት በድል የመጠናቀቁ ብስራት በኩራዝና ጭስ የሚሰቃዩ እናቶችን ተስፋ ያፈነጠቀ አኩሪ የታሪክ አሻራ ነው ያሉት ሰልፈኞች፥ ተስፋ ሊያስቆርጡ የሚከጅሉ የውጭ ኃይሎችና የውስጥ ተላላኪዎች የህዝቡን አንድነት አይተው ያፍራሉም ነው ያሉት።
በአባይ ግድብ የታየውን መተባበርና አንድነት ዛሬም በሀገር አውዳሚ ርዝራዥ ጁንታ ላይ በመድገም ብልጽግናችንን እናስቀጥላለንም ብለዋል፡፡
በመለሰ ታደለ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

