Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሀረሪ ክልል የፊታችን ሃምሌ 20 መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍና ህወሓትን የሚቃወም ህዝባዊ ሰልፍ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ፣ሃምሌ 18፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀረሪ ክልል የፊታችን ሀምሌ 20 ቀን 2013 ዓ.ም መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ እና አሸባሪው ህወሓትን የሚቃወም ህዝባዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

የክልሉ ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ደጀንነት ለመግለጽ ፣ የውጪ ሀይሎች በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ የሚያደረጉትን ጣልቃ ገብነት እና አሸባሪው ህወሓትን በመቃወም በተጠቀሰው ቀን ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚካሂዱ የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ህዝባዊ ሰልፉ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ በሀረር ኢማም አህመድ ስታድየም የሚካሄድ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ ገልጸዋል።

ሰልፉ የሕዝቡን ጥያቄ መሠረት በማደረግ የሚካሄድ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው÷  ጁንታውን ከመቃወም ባለፈ ሕዝቡ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያለውን ደጀንነት ለመግለጽ ያለመ መሆኑን መናገራቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁ እና የሕዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መከናወኑን ጨምሮ እስካሁን በሀገር ደረጃ የተገኙ ድሎች የሚወደሱበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

Exit mobile version