Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አመታዊው የቁልቢ ገብርኤል ንግስ በዓል በሰላም ተከብሯል- ፖሊስ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 19፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)አመታዊው የቁልቢ ገብርኤል ንግስ በዓል ዛሬ በሰላም መከበሩን ፖሊስ አስታወቀ።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ድቪዥን ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ቶሎሳ ጎሹ እንደገለጹት፥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኦርቶዶክስ ሀይማኖት ተከታዮች የታደሙበት አመታዊው የቁልቢ ገብርኤል ንግስ በዓል ያለ ጸጥታ ችግር በሰላም ተከብሯል።

በአካባቢው የተቋቋመው የጸጥታ አካል ባካሄደው አስቀድሞ የወንጀል መከላከል ስራና ህብረተሰቡ በመገናኛ ብዙሀንና በተለያዩ ዘዴዎች የተሰጠውን መልዕክት ተቀብሎ ባደረገው ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ በአሉ በሰላም ሊከበር መቻሉን ተናግረዋል።

ወጣቶችን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች ለምዕመናን ያደረጓቸው አቀባበልና የመስተንግዶ ስነ ስርዓት በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ጉልህ አስተዋፅኦ ማድረጉን ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በንግስ በዓሉ የተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ሰርቀው እጅ ከፍጅ የተያዙ አምስት ግለሰቦች በበአሉ ስፍራ በተቋቋመ ጊዜያዊ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው በምርመራ ተጣርቶ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ መደረጉን ገልጸዋል።

ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮቹ ለተሰረቁባቸው ባለንብረቶች እንዲመለሱ መደረጉንም ተናግረዋል።

ምዕመኑ ወደ ንግስ በዓሉ መምጣት ከጀመሩበት ከባለፈው አርብ ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ ምንም ዓይነት የተሽከርካሪ አደጋም ሆነ ግጭት አለመድረሱን አመልክተዋል።

ምእመናን ከበዓሉ በኋላ ወደየ አካባቢያቸው ሲመለሱ ከዚህ ቀደም ያሳዩትን የትራፊክ ህግ ስነስርዓት አከባበር እንዲደግሙ ዋና ኢኒስፔክተሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በተመሳሳይ የቅዱስ ገብርኤል የንግስ በዓል በሀዋሳ ከተማ በሰላም ተጠናቋል፡፡

በዚህ ዓመት በክብረ በዓሉ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሐይማኖቱ ተከታይ ምዕመናንና እንግዶች የተገኙ ሲሆን፥ የንግስ በዓሉን ምክንያት በማድረግም ምዕመኑ ለሀገር ሰላም እንደሚፀልዩ ገልፀዋል፡፡

በዓሉ ከመንፈሳዊ ሥርዓትነቱ በተጨማሪ በከተማዋና በአጎራባች አካባቢዎች ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ መፍጠር የቻለና ማህበረሰቡም ተጠቃሚ የሆነበት እንደነበረ ነው የተገለፀው፡፡

በታምራት በጋሻው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version