አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 21 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ልዩነቶች ሳይበግሩን አሸባሪውን ሕወሓት ለአንድ ጊዜ እና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ ይገባል ሲሉ ተናገሩ።
የአማራ ክልል መንግሥትን የክተት ጥሪ በመቀበል በዛሬው ዕለት በባሕር ዳር ከተማ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
በባሕር ዳር ከተማ የተካሄደው ሕዝባዊ ሰልፍ የመጀመሪያው ዓላማ አሸባሪው ሕወሓት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠላት መሆኑን ሕዝቡ አቋሙን የገለጸበት እንደሆነ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ለዚህ ሀገር አፍራሽ ቡድን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ድጋፍ ለሚያደርጉ ሀገራት ለአሸባሪ ድጋፍ ከመስጠት እጃቸውን እንዲሰበስቡ ታላቅ መልእክት የተላለፈበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
አሸባሪው ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው ክህደት እና ዘግናኝ ግፍ እንዲሁም በማይካድራ የፈፀመው የዘር ማጥፋት ድርጊት ታሪክ የማይረሳው ድርጊት ነው ብለዋል ምክትል ከንቲባው። ይህ ሳይበቃው ዛሬም በአፋር እና በአማራ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ጦርነት መክፈቱን ገልጸዋል።
በተለይም ከአማራ ሕዝብ ጋር የማወራርደው ሒሳብ አለኝ በሚል ልክ እንደ ድሮው የኢትዮጵያን ሕዝብ በመከፋፈል ኢትዮጵያን የማፈራረስ ዓላማውን ለማሳካት ቢጥርም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ያገኘው ምላሽ ተቃራኒ እንደሆነ ተናግረዋል።
ዛሬ የመላው ኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የሕወሓትን ሴራ ተገንዝበው በአማራ እና አፋር ክልል ድንበር እየፈፀመ ያለውን ጥቃት ለመመከት ወደ ግንባር እየተመሙ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሴራ ተወልዶ በሴራ ያደገው ሕወሓት የሚዋጋው ብቻውን ሳይሆን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሌት ተቀን ከሚታትሩ የሀገራችን ታሪካዊ ጠላቶች ጋር እንደሆነም አስገንዝበዋል።
የውጭ ኃይሎች የተፅዕኖ በትራቸውን ኢትዮጵያ ላይ ለማሳረፍ ሕወሓትን እንደ ፈረስ እንደሚጠቀሙበት የጠቀሱት ከንቲባው፣ ዛሬ ላይ ለሽብርተኛው ሕወሓት ጠበቃ እስከመሆን የደረሱትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን አመላክተዋል።
ስለሆነም የአርበኝነት ገድል ለመፈፀም የክተት ጥሪውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበል ይገባል ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

