Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በዳውሮ ዞን የአረንጓዴ አሻራቸውን አሳረፉ

አዲስ አበባ ፣ሐምሌ 21፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በደቡብ ክልል በዳውሮ ዞን ሎማ ወረዳ ተገኝተው በክልሉ የተካሄደውን የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ በመቀላቀል ችግኝ ተከሉ።

በመርሃ ግብሩ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እና የመስሪያ ቤቱ የስራ ሀላፊዎች በታላቁ ኦሞ – ጊቤ ተፉሰስ ውስጥ በጊቤ 3 ግድብ ንኡስ ተፋሰስ ተገኝተው ችግኝ ተክለዋል፡፡

መርሃ ግብሩ ተከላው በመላው ሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያን አረንጓዴ እና ልብሳት መርሃ ግር እንዲሁም በክልሉ የተካሄደው የአንድ ጀምበር ተከላ አካል መሆኑን ኢንጂነር ስለሺ ገልፀዋል፡፡

አያይዘውም በአካባቢው የገበታ ለሃገር ፕሮጀክት ክላስተር ያለበት በመሆኑ የአረንጓዴ አሻራ ስራውን ከልማት ፕሮጀክቶች ጋር በማስተሳሰር መሰራቱ ውጤታማነቱን ዘርፈ ብዙ ያደርገዋልም ብለዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የውሃ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ መሰል የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች በዳውሮ ማህበረሰብ በአካባቢ ጥበቃ ረገድ ያለውን መልካም እሴት የሚያጎለብት እንደሆነ ጠቁመዋል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ ብሄራዊ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄም በችግኝ ተከላው የተሳተፉ ሲሆን ሁሉም ሰው የተተከሉ ችግኞችን ሊጠብቅ እንደሚገባ አውስተዋል፡፡

ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደቡብ ክልል 1 ነጥብ 538 ቢሊየን ችግኞች ያዘጋጀ ሲሆን የአንድ ጀምበር ተከላውን ጨምሮ እስካሁን ከ971 ሚሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ከውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version