አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 21፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ለ2014 በጀት ዓመት 4 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት በማጽደቅና ውሳኔዎችን በማሳለፍ ጉባኤውን አጠናቀቀ፡፡
በክልሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶችን በማሳካት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ጠንክረው እንዲሰሩ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ጁል ናንጋል አሳስበዋል ።
ጉባኤው በሶስት ቀናት ቆይታው የክልሉ 2013 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም፣ የ2014 የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ፣ የማስፈፀሚያ በጀት፣ ረቂቅ አዋጅና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቶ አጽድቋል።
እንዲሁም የስነ ምግባርና የአቅም ችግር ያለባቸውን የአምስት የዞንና የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች ሹመትን አንስቷል።
የክልሉን የ2014 በጀት አመት 4 ቢሊየን ብር የሚጠጋ በጀት አጽድቋል።
ከጸደቀው በጀት 1 ቢሊዮን 167 ሚሊዮን ብሩ ከክልሉ የተለያዩ የገቢ ምንጮችና ቀሪው 2 ቢሊዮን 827 ሚሊዮን ብር ከፌዴራል መንግስት ድጎማና ከወጪ በሚገኝ ብድርና እርዳታ የሚሸፈን መሆኑ ተመላክቷል።
ለበጀት ዓመቱ የጸደቀው ማስፈጸሚያ በጀት ከ2013 በጀት አመት ጋር ሲነፃፀር ከ657 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው መጠቀሱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ጁል ናንጋል በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ እንዳሉት÷የታቀዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶችን በማሳካት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል።
“እንደ ሀገር በህወሓት ጁንታ የተቃጠውን ዘመቻ በመመከት የተጀመሩ የልማት እቅዶችን በማሳካት የብልጽግና ጉዞውን ለማስቀጠል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ ይገባል “ብለዋል።
በተጠናቀቀው 2013 በጀት ዓመት የህዝቡን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ የተከናወኑ ስራዎች አበረታች እንደነበሩ በጉባኤው መገንዘብ መቻሉን ተናግረዋል።
በቀጣይም በተጠናቀቀው በጀት አመት የተገኙትን መልካም ተሞክሮች በማስፋትና ደካማ ጎኖችን በማረም የጸደቁትን የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶችን ለማሳካት አመራሩ የህዝቡን ተሳተፎ በማጠናከር በትጋት እንዲሰራ አስገንዝበዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
