አዲስ አበባ ፣ሐምሌ 21፣ 2013 ( ኤፍ ቢ ሲ) ሸበሌ የተባለች የኢትዮጵያ መርከብ ከ11ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ ስኳርና ሩዝ ይዛ በርበራ ወደብ መድረሷን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ፥መርከቧ ከህንድ የጫነችውን ስኳርና ሩዝ ይዛ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ድርሻ ባላት የበርበራ ወደበ እያራገፈች ነው።
በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ታሪክ የኢትዮጵያ መርከቦች ወደ በርበራ ወደብ ጉዞ ሲያደርጉ ከ 20 ዓመታት በኋላ ሸበሌ መርከብ ሁለተኛ ናት።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በበርበራ ወደብ የተጀመረው አገልግሎት የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
የሱማሌላንድ ነጋዴዎች ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸውን የገለጸው ድርጅቱ፤ አገልግሎት መስጠቱን በመደበኛነት እንደሚቀጥል ገልጿል።
ጊቤና ሸበሌ የተባሉት መርከቦች በኮሪደሩ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ መሆናቸውንም የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገልጿል።
በነሐሴ ወር አጋማሽ ጊቤ መርከብ 15ሺ ሜትሪክ ቶን ሩዝ በመጫን በርበራ ወደብ እንደምትገባ ድርጅቱ ስለመግለጹ ከትራንስፖርት ሚንስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።