Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ፋይናንሺያል ታይምስ የትግራይን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ያወጣው ዘገባ ሚዛናዊነት የጎደለው እና ለህወሓት ያደላ ነው

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 23፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋይናንሽያል ታይምስ የትግራይን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ያወጣው ዘገባ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጥቃት በመሰንዘር የግጭቱ ጠንሳሽ መሆኑን ያላሳየ፣ የተኩስ አቁሙን በመጣስ ህጻናትን ሳይቀር ወደ ጦርነት ማስገባቱን እና መሬት ላይ ያለውን ሃቅ የማያሳይ መሆኑ ተገለጸ።

በአሜሪካ የኢትዮጵያውያን ጉዳዮች ኮሚቴ ፋይናንሽያል ታይምስ የትግራይን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ያወጣውን ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ አስመልክቶ  የተቃውሞ ደብዳቤ ለተቋሙ ጽፏል።

ኮሚቴው በደብዳቤው  ድርጅቱ ባወጣው ዘገባ ሰብዓዊ ድጋፍና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ ለመንግስት ያቀረበውን ጥያቄ ለምን ለአሸባሪው የህወሓት ድርጅት አላቀረበም ሲል ሞግቷል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በጥቅምት 24 ቀን  2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በማድረስ ግጭቱን እንደጀመረ ለምን በዘገባው አልተካተተም ሲልም ይጠይቃል፡፡

መንግስት በቅርቡ የተናጠል ተኩስ አቁም ቢያደርግም አሸባሪው ቡድን ተኩስ አቁሙን ሲጥስና ወደ አጎራባች ክልሎች ጥቃት ሲሰነዝር ለምን በዘገባችሁ አላካተታችሁም ሲል አመልክቷል።

የሽብር ቡድኑ ህጻናትን ወደ ጦርነት ሲያስገባና አለም አቀፍ ህግን ሲጥስ የምርመራ ዘገባችሁ በዚህ ላይ ለምን ጥያቄ አላነሳም በማለት ሞግቷል።

ምዕራባውያን በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ላለቸው ፍላጎት ወሳኝ ቀጠና በሆነው አካባቢ ላይ ለአንባቢዎች ሚዛናዊ ዘገባ ሊደርሳቸው እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጾ፤ የተሳሳተና ሚዛናዊ ያልሆነውን ዘገባ ፋይናንሽያል ታይምስ እንዲያርመው ጠይቋል።

Exit mobile version