አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 3፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በ2013 በጀት ዓመት ሀብታቸውን በትክክል ስለማስመዝገባቸው የማረጋገጥ ሥራ ከተሰራባቸው ሀብት አስመዝጋቢዎች መካከል 47 በመቶ የሚሆኑት ያስመዘገቡት የሀብት መረጃ የተሳሳተ መሆኑን የፌደራል የስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 668/2002 አንቀጽ 11 መሰረት ኮሚሽኑ በ2013 በጀት ዓመት ለሙስና ተጋላጭ በሆኑ ዘርፎች ላይ በሚሰሩ 386 ሀብት አስመዝጋቢዎችና ቤተሰቦቻቸው ላይ የሀብት ምዝገባ ትክክለኛነትን የማረጋገጥ ሥራዎች መስራቱ ተገልጿል፡፡
በበጀት ዓመቱ የመረጃ ትክክለኛነትን የማረጋገጥ ተግባር ከተከናወነባቸው ሀብት አስመዝጋቢዎች መካከል 47 በመቶ የሚሆኑት ያስመዘገቡት ሀብት ትክክለኛነት የጎደለው መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
አብዛኛዎቹ ሀብት አስመዝጋቢዎች ባስመዘገቡት ሀብት ላይ መጠነኛ ልዩነት የተስተዋለባቸው በመሆኑ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው እንዲያስተካክሉ መደረጉ ተመላክቷል፡፡
13 ሀብት አስመዝጋቢዎች ደግሞ ባስመዘገቡት ሀብትና ባላቸው ሀብት መካከል ያለው ልዩነት ከፍተኛ በመሆኑ በሕግ እንዲጠየቁ ለተጨማሪ ምርመራ መረጃዎቻቸው ለፍትህ አካላት መላካቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታለል፡፡
በተካሄደው የሀብት ምዝገባ መረጃ ትክክለኛነት የማረጋገጥ ሥራ ከተገኙ ልዩነቶች መካከል በአንድ ግለሰብ ስም ሳይመዘገብ የቀረ በተለያዩ የሂሳብ ቁጥሮች ከ4 ሚሊየን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ መገኘቱ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም አንድ ግለሰብ ሳያስመዘግባቸው የቀረ 4 መኖሪያ ቤቶች፣ ተሽከርካሪ እና ሌሎችም ግኝቶች የታዩ እና ግኝቶቹም በሀብት ምዝገባ ወቅት አስመዝጋቢዎቹ ሳያስመዘግቧቸው የቀሩ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

