Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሽብር ቡድኖቹ ግጭት ለመፍጠር ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ ተብለው በተለዩ ቦታዎች ላይ ጠንካራ አደራጃጀት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራልና የአማራ ክልል የስራ ኃላፊዎች የሰሜን ሸዋ ዞን አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ጋር የህወሓትና የሸኔ የሽብር ቡድኖችን መቆጣጠር የሚያስችል አደረጃጀት እየፈጠሩ መሆኑ ተገለጸ፡፡
 
ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ የሚቻልበት አሰራር እየተዘረጋ የሚገኘው በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሞ ብሄረሰብ አሰተዳደር ዞን፣ በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን እንዲሁም በአፋር ክልል ዞን 5 መሆኑ ተመላክቷል፡፡
 
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሃመድ ከዚህ በፊት የብሄር ግጭት ለመፍጠር ቡድኖቹ ሲሰሩ የቆዩባቸው የአማራ፣ የአፋርና የኦሮሚያ ክልል አጎራባች ዞኖች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል ስርዓት እየዘረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
 
የሽብር ቡድኖቹ ግጭት ለመፍጠርና ጥቃት ለመፈፀም የሚችሉባቸውን ቀዳዳዎች በሙሉ ለመድፈን እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ህብረተሰቡ ከወተሮው በተለየ ንቁ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
 
የአማራ ክልል የኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ የሶስቱ ክልሎች ጥምረት በግምባር ያለውን ድል ከማፋጠን ባለፈ የክልሎቹን የእርስ በእርስ ትስስር እንደሚያጠናክረው ገለፀዋል።
 
የሶስቱ ክልሎች ቅንጅታዊ አሰራርም የሽብር ቡድኖቹን ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ የሚደረገውን ጥረት ያፋጥነዋል ብለዋል።
 
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍቅረማርያም ደጀኔ በበኩላቸው በዞኑ የተዘረጋው የሶስቱ ክልሎች አደረጃጀት ሰርጎ ገቦችን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ከማስቻሉም በላይ በቀጣይ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠርም መተዋወቅን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
 
የስራ ኃላፊዎቹ በቀጠናው ከሚገኙ ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ ከተሞችና ቀበሌዎች አመራርና ከፀጥታ ኃይሎች በመምከር የተለያዩ አደራጃጀቶችን መፍጠራቸውን ከሰሜን ሸዋ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
በቀጣይም በሌሎች አካባቢዎች በመዘዋወር የሽብርተኛ ቡድኖችን ሰርጎ መግባት ለመከላከል የሚያስችሉ ስልጠናዎችን በመስጠት አደራጃጀቶችን ለመፍጠር ይንቀሳቀሳሉ ተብሏል።

 

ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version