Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

32 የአሻባሪው ህወሓት ተላላኪዎች በቁጥጥር ሰር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብርተኛውን ህወሓት ቡድን ጥፋት ለማስፈጸም ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሲገቡ የነበሩ 32 የጥፋት ተላላኪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አብልአዚም መሃመድ እንደገለጹት በቁጥጥር ስር የዋሉት በሽብርተኛው የህወሓት አስተባባሪነት ከሃገር ውጭ ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ ናቸው፡፡
ግለሰቦቹ በክልሉ ጠረፍ አካባቢ አሶሳ፣ ኩርሙክ ወረዳዎች በኩል ድንበር አቋርጠው ባለፉት ሶስት ተከታታይ ቀናት ወደ ክልሉ ሲገቡ መቆጣጠር መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት አብዛኞቹ ወጣቶች ሲሆኑ በሽብርተኛው ቡድን “የፌደራል መንግስት ተዳክሟል” በሚል የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ተታልለው ወደ ጥፋት መንገድ የገቡ ናቸው ብለዋል፡፡
እንዲሁም በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ሲሳተፍ የነበረው የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤህነን) ምክትል አመራር እና ፓርቲውን ወክለው በምርጫ የተሳተፉ እጩዎች፣ አሶሳ ከተማ ተቀምጦ ጥፋቱን ሲያስተባብር የነበረ የአሸባሪው አባል እንደሚገኙበት አብራርተዋል፡፡
የጥፋት ቡድኑ ተላላኪዎች የያዙት የጦር መሣሪያ፣ ቢላዋ፣ ገጅራ፣ ላፕቶፕ ካምፒዩተር፣ የባንክ ደብተር እና ሌሎችም ቁሳቁሶች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ግለሰቦቹን መቆጣጠር የተቻለው በአካባቢው ማህበረሰብ ፣ሃገር መከላከያ እና ክልሉ ልዩ ሃይል እንዲሁም ሚኒሻ አባላት ጋር ባረጉት የተቀናጀ ጥረት መሆኑን አንስተው ህብረተሰቡም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version