Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጨምሮ በሽብር ወንጀል የተከሰሱ 41 ተከሳሾችን ፌዴራል ፖሊስ  ለህግ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ  ትእዛዝ አስተላለፈ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ፣አቶ ጌታቸው አሰፋ፣አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በሽብር ወንጀል የተከሰሱ 41 ተከሳሾችን ፌዴራል ፖሊስ ከመከላከያ ጋር በመተባበር ለህግ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ አስተላለፈ።

በሽብር ወንጀል ክስ ከተመሰረተባቸው 62 ተከሳሾች ውስጥ 21ዱ ፍርድ ቤት ቀርበው የተከሰሱበት ክስ በንባብ ቀርቦላቸዋል።

ዛሬ ፍርድ ቤት ከቀረቡት ውስጥ ለ19ኙ ተከሳሾች ክሱ ከዚህ ቀደም በፅሁፍ በእጃቸው እንዲደርሳቸው መደረጉ የተገለጸ ሲሆን ÷ ለሁለቱ ተከሳሾች ደግሞ ዛሬ ክሱ ደርሷቸዋል።

በተጨማሪም  አቃቢ ህግ ያሉትን ማስረጃዎች በፍላሽ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

አቶ ስብሀት ነጋ ፣ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሄም፣ዶክተር አብርሀም ተከስተ፣አምባሳደር አባይ ወልዱ፣ዶክተር ሰሎሞን ኪዳኔ፣ወይዘሮ ሙሉ ነጋን ጨምሮ 21 ተከሳኞቹ እያንዳንዳቸው የተሳተፉበት ወንጀል እና ክስ በዝርዝር ተነቦላቸዋል።

50 ገፅ ያለው እና ዛሬ በችሎቱ በተነበበው ክስ ላይ አቃቤ ህግ  በተከሳሾች ላይ ሁለት ክሶችን  መመስረቱ ተገልጿል።

ይህም በሀይል እና በህገወጥ መንገድ የክልል መንግስትንና የፌዴራል መንግስትን  ለመለወጥና  የሽብር ጥቃት መፈፀም በሚሉት ሁለት የሽብር ወንጀል ነው አቃቢ ህግ  ክሶችን ነው የመሰረተባቸው።

በእነዚህ ክሶች ውስጥም የተፈፀሙ ዝረዝር ወንጀሎች በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ የደረሱ ጉዳቶችን ጨምሮ የተፈፀሙ ጥቃቶች ተካተዋል።

ክሱ በንባብ ከቀረበ በኋላም የዋስትና ጥያቄ ላይ በአቃቤ ህግ እና በተከሳሾች ጠበቆች መካከል ክርክር ተካሂዷል።

ከሳሽ አቃቤ ህግ አብዛኞቹ ተከሳሾች በሁለት ክስ የተከሰሱ በመሆናቸው፣ተከሳሾቹ የፈፀሙት የሽብር ወንጀል ከእድሜ ልክ እስራት እስከ ሞት የሚያስቀጣ ፣ የፈፀሙት ወንጀልም ከፍተኛ ነው የሚሉ እና ተከሳሾቹ ዋስትና እንዳያሰጣቸው የሚያደርጉ ሀሳቦችን ከተቀመጡ የወንጀል መቅጫ ህጎች እና አዋጆች ጋር አጣምሮ አቅርቧል።

የተከሳሾቹ ጠበቆችም የዋስትና መብታቸው ሊከበር ይገባል በማለት አቃቤ ህግ ባቀረባቸው ሀሳቦች ላይ መከራከሪያዎችን ለችሎቱ አቅርበዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ በዋስትና ክርክር ላይ ብይን ለመስጠት ለሀሙስ ነሀሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

አንደኛ ተከሳሽ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዛብሄር፣አራተኛ ተከሳሽ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ስድስተኛ ተከሳሽ አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ያልተያዙ 41 ተከሳሾች ፍርድ ቤት ያልቀረቡ በመሆናቸው ፌዴራል ፖሊስ እነዚህን ተከሳኞች ይዞ እንዲያቀርብም ችሎቱ አዟል።

በዙፋን ካሳሁን

ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version