አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በህግ ማስከበር ስራ ላይ ላለው የመከላከያ ሰራዊት ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የገንዘብ እና የደም ልገሳ ድጋፍ ማድረጉን ገለፀ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን÷ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን በጥሬ ብር እና ቀሪው 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ደግሞ ምግብ ነክና የህክምና ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ተወካይ አቶ ሳላህ ሁሴን ገልፀዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት በኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመቀልበስ እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት ከተደረገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ሰራተኞች የአንድ ወር ደሞዝና ደም ልገሳ አከናውነዋልም ነው ያሉት፡፡
ግንባር ድረስ በመሄድ በሙያቸው ለማገልገል ቁርጠኝነት ያሳዩ ሰራተኞች መኖራቸውንም አቶ ሳላህ ተናግረዋል፡፡
ሰራተኞች በበኩላቸው ህወሀት ባለፉት 30 አመታት በሰራቸው ግፎች እንደ ሶማሌ ክልል ተወላጅ ብዙ ግፍ ተሰርቶብናል፤ ክልሉም በልማት ወደኋላ እንዲቀር ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
አያይዘውም ችግሩን አሳንሶ ከማየት ይልቅ ሁላችንም መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና ወስደን ለማንኛውም ሁኔታ ራሳችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል ብለዋል፡፡
በብስራት መለሰ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

