አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በባህሬን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በክር ከባህሬን የሰራተኛና ማህበራዊ ልማት ሚኒስትር ጀሜል ቢን መሐመድ አል ሁሜዳን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም የሁለቱን አገራት ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ተገልጿል፡፡
በዚህ ወቅት አምባሳደር የባህሬን መንግስት በአገራቸው ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እና ትብብር አድንቀዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በባህሬን ህጋዊ የሰው ኃይል የስራ ስምሪት እንዲኖር ከዚህ ቀደም የተለዋወጥናቸውን የሰራተኛ ስምሪት ስምምነት ወደ ተግባር በሚገባበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም የባህሬን መንግስት በአገራቸው ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተሰጠውን ምህረት አዋጅ አድንቀው፥ በውይይቱም ይህን እድል ዜጐቻችን ያልተጠቀሙ በመሆኑ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ለሌላቸው ኢትዮጵያዊያን ምህረቱ በድጋሚ እንዲደረግላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በባህሬን አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሰብዓዊ መብታቸውና ጥቅማቸው እንዲከበርላቸው እንዲሁም አልፎ አልፎ የሚከሰተውን ችግር እንዲፈቱላቸውም ትብብር ጠይቀዋል፡፡
ጀሜል ቢን መሐመድ አል ሁሜዳን በበኩላቸው ፥ በሁለቱ ሀገራት መካከል የህዝብ ለህዝብ ትብብርና መልካም ግንኙነት እንዲጠናከር ለማድረግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የተለዋዋጥናቸውን የሰራተኛ ስምሪት የመግባቢያ ሰነድ እያዩትና በቅርብ ተጠናቆ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ፍላጐታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብንና የባህሬን ህዝብን ብዙ የሚያቀራርባቸው ባህል ሃይማኖትና ማህበራዊ ትስስር በመኖሩ ለቀጣይ ይበልጥ እንዲጠናከር ለማድረግ ስምምነቱን ወደ ተግባር መግባት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡
ምህረቱን በተመለከተ በድጋሚ ለኢትዮጵያዊያን ምህረት እንዲደረግ ከዚህ በፊት የቀረበውን ጥያቄ እያዩት መሆኑንና ምላሻቸውን በቅርቡ እንደሚያሳውቁ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

