Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የህወሓት አሸባሪ ቡድን በሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪዎችን ምንነቱ ያልታወቀ መርፌ ወግቷል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የህወሓት አሸባሪ ቡድን በሰሜን ወሎ ዞን ሃብሩ ወረዳ ነዋሪዎችን ምንነቱ ያልታወቀ መርፌ ሲወጋ ማየቱን አንድ የአይን እማኝ ገለጸ።
 
በሀብሩ ወረዳ ቀበሌ 020 የሚኖረው ወጣት መሀመድ አንሷር እንዳለው የህወሓት አሸባሪ ቡድን በአካባቢው ሰርጎ ከገባ በኋላ የተለያዩ የግልና የህዝብ ንብረቶችን ዘርፏል።
 
በየደረሱባቸው አካባቢዎች ሁሉ ዘርፎ የሚፈልገውን ያክል ከጫነ በኋላ ሌላውን በማቃጠል ሲያወድም ተመልክተናል ብሏል።
 
ከዚህ ባለፈም “የኮቪድ19 መከላከያ ነው” በሚል አሸባሪው ቡድን የተለያዩ ሰዎችን መርፌ ሲወጋ ተመልክቻለሁ ብሏል መሀመድ።
 
አሸባሪ ቡድኑ ሰዎችን የሚወጋው መርፌ እስካሁን ምን እንደሆነና ለምን ዓላማ እንደሆነ ባይታወቅም “መርፌ የተወጋ እርዳታ ያገኛል” በሚል በርካታ ሰዎችን ወግቷል ነው ያለው።
 
በተመሳሳይ በአፋር ክልል መርፌ ተወግቶ የእርዳታ አህል ያገኘ ጓደኛዬ አለ ሲልም መሃመድ ተናግሯል።
 
የአሸባሪው ህወሓት ዘራፊዎች በገቡባቸው አካባቢዎች ሁሉ ቤት ሲያቃጥሉ ንጹሃንን ሲገድሉ ማየቱንም ተናግሯል።
 
የአሸባሪው ቡድን ዘራፊዎች ለሰው ልጅ ምንም አይነት ርህራሄ የሌላቸው ጨካኞች መሆናቸውን በሚፈፅሟቸው ግዲያዎች ተመልክተናል ብሏል መሀመድ።
 
በተለያዩ አካባቢዎች የአርሶ አደሮችን ቤት በማቃጠልም በጭካኔ ንብረቶችን ሲያወድሙ ተመልክቻለሁ ሲል እማኝነቱን ገልጿል።
 
የአርሶ አደሮችን የቤት እንስሳቶች እየዘረፉ በማሸሽና ከባድ በደል በመፈፀም ላይ ይገኛሉም ነው ያለው።
 
ለትግራይ ክልል ነዋሪዎች የጥሞና ጊዜ ለመስጠት መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ቢያደርግም የህወሓት አሸባሪ ቡድን ሰርጎ ገቦች በአማራ እና አፋር ክልሎች ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስና ውድመት እያስከተሉ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version