አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በምርት ዘመኑ 131 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት አቅዶ እየሰራ መሆኑን የአማራ ክል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
በዚህም የምግብ፣ የኢንዱስትሪና የኤክስፖርት ሰብሎችን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑም ነው የተገለፀው፡፡
የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ በተለይም የዱቄት፣ የፓስታና ዘይት ፋብሪካዎች እየተስፋፉ መሆናቸውን ተከትሎ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡
በዚህም በቅርቡ ስራ ለጀመሩት የዘይት ፋብሪካዎች ግብዓት ሆኖ የሚያገለግለው የአኩሪ አተር ሰብል ምርት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ ተናግረዋል፡፡
በተያዘው ዓመትም ከተለመደው አሠራር በመውጣት የፓኬጅ ስልጠናና የህያው ማዳበሪያ አቅርቦት ስራ መሰራቱን ነው የተናገሩት፡፡
በአርሶ አደሩና በባለሀብቱ ከ85 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታገጠም እርሻ መልማቱን ምክትል ሃላፊው አቶ ተስፋሁን ገልፀዋል፡፡
በክልሉ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በምዕራብ ጎንደር፣ በማዕከላዊ ጎንደርና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች አኩሪ አተር በስፋት የሚመረት ሲሆን÷ በ2013/14 ምርት ዘመን ከሁለት ሚሊየን ኩንታል በላይ አኩሪ አተር ይመረታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምክትል ቢሮ ሀላፊው መናገራቸውን ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

