አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በባህሬን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በክር ከባህሬን የባህልና ቅርስ ባለስልጣን ፕሬዚዳንት ከሆኑት ሜይ ቢንት መሐመድ አልከሊፋ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች ባህል፣ ትውፊትና ግንኙነት በሚያጠናክሩበት ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
አምባሳደር ጀማል በክር ኢትዮጵያ ባለብዙ ባህል፣ አርትና ሙዚቃ አርኪዮሎጂ፣ ታሪክ ባለቤትና ቀደምት ስልጣኔ ያላት አገር በመሆኗ ን ገልጸዋል።
በዚህ ዘርፍ ይበልጥ ከባህሬን ጋር በቅንጅትና በትብብር የሚሰራበት ነጥቦች ናቸው ብለዋል ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ የተለያዩ እምነቶች ባለቤት፣በቅርብና በሩቅ ካሉት አገራት ጋር የሚያስተሳስር የአብሮነትና የትብብር ተምሳሌት በመሆኗ፥ ይህ እሴትና ባህል እንዲጠናከር ለማድረግ የሁለቱ አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ትብብር ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
በተያያዘም የባህሬን የባህልና የቅርስ ባለስልጣን ከአቻው የኢትዮጵያ የምርምርና የባህል ቅርስ ባለስልጣን ጋር በትብብር ሊሰሩ የሚችሉበትን ሁኔታ አንስተው ተወያይተዋል፡፡
የባህሬን የባህልና የቅርስ ባለስልጣን ፕሬዚዳንት ሜይ ቢንት መሐመድ አልከሊፋ በበኩላቸው፥ ስለተደረገላቸው ገለፃ አመስግነው፥ ኢትዮጵያ ቀደምት የታሪክ፣ የቅርስና የባህል ባለቤት በመሆኗ በዚህ ዘርፍ ብዙ ተሞክሮ ልታበረክት የምትችል አገር መሆኗን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የባህል ፣ አርትና የሙዚቃ ዝግጅቶች የተዘጉ ቢሆንም በቅርቡ የተለያዩ ዝግጅቶች የሚጀምሩ በመሆኑ የኢትዮጵያ ባህል፣ አርትና ሙዚቃ ለማስተዋወቅ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማትና ከቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ጋር በቅርበት ለመስራት ፍላጐታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በባህሬን ያሉ ኢትዮጵያዊያን ባህላቸውን ለማስተዋወቅ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ባለሥልጣኑ በሙሉ አቅም የሚደግፋቸው መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

