አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከናይል የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በወቅቱም አምባሳደር ሬድዋን ኢትዮጵያ በናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም መርህ እንዲሰፍን ጠንካራ አቋም በመያዝ ከተቀሩት የተፋሰሱ ሀገራት ጋር በቅርበት ስትሰራ መቆየቷንና ይህንኑ ለማጠናከር የሚያስችል የምክክር ጉባኤ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
አምባሳደሩ አያይዘውም የናይል አጠቃላይ ስምምነት ማዕቀፍን የፈረሙ፣ ያፀደቁ እንዲሁም ያልፈሩሙና ያላፀደቁ የላይኛው ተፋሰስ አገራት መኖራቸው አስታውሰው፣ ያልፈረሙና ያላፀደቁ አገራት እንዲፈርሙና እንዲያፀድቁ አስፈላጊው ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የላይኛው ተፋሰስ አገራት አምባሳደሮችም በበኩላቸው፥ በቀረቡት ሃሳብ ላይ በመንተራስ ድንበር ተሻጋሪ ሃብቶችን ለጋራ ልማት ለማዋል የጋራ ትብብር እንደሚያስፈልግ እንዲሁም የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካዊያን መፍታት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
ቱኒዚያ ለተባበሩት የፀጥታው ምክር ቤት ለግብጽ ተገቢ ያልሆነ ድጋፍ ለማድረግ ያቀረበችው የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ ቢደረግባትም በድጋሚ ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጓን ሚኒስትር ዴኤታው አንስተው፥ ይህ ውሳኔ ቢወሰን የሁሉም የላኛው ተፋሰስ አገራት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሊያስገባ እንደሚችልና ይህን ሃሳብ ለመቀልበስ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ በገለጻቸው አሳስበዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን አክለውም የቱኒዚያ አካሄድ በአፍሪካ ህብረት እየተመራ ያለውን የሶስትዮሽ ድርድር ጥረት የሚያደናቅፍ መሆኑን ገልጸው፥ አገራቱ ኒውዮርክ ለሚገኙት ሚሲዮኖቻቸው ይህንኑ እንዲገልጹላቸው መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽኅፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

+3
0
People Reached
228
Engagements
Boost Post
213
3 Comments
12 Shares
Like
Comment
Share

