አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ህዝብ ከ6ሺ ሄክታር በላይ የዘማች ቤተሰቦች መሬትን አርሶ በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ ገለጹ ።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ነጋ ይስማው÷በዘንድሮ የመኸር እርሻ በህልውና ዘመቻው የሚሳተፉ የዘማች ቤተሰቦች መሬትን በዘር በመሸፈን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም የማዕከላዊ ጎንደር ህዝብ 12 ወረዳዎችና ሶሰት የከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ የዘማች ቤተሰቦች ይዞታ የሆነ 6ሺ 609 ሄክታር የእርሻ መሬት በወቅቱ አርሶ በመዝራት እየተንከባከብ ነው።
ለዘማች ቤተሰቦች የጉልበት አስተዋጽኦ ካበረከተው ህዝብ መካከልም ወጣቶች፣ ሴቶችና የመንግስት ሰራተኞችና የግብርና ባለሙያዎች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስዱ ነው ሃላፊው ያስታወቁት።
ህዝቡ በሐምሌና ነሐሴ ወራት ለዘማች ቤተሰቦች የግብርና ስራ በማገዝ ያበረከተው የጉልበት አስተዋጽኦ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ገልጸዋል፡፡
መምሪያውና በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ጽህፈት ቤቶች የዘማች ቤተሰቦች በአነስተኛ ወለድ የአፈር ማዳበሪያ ቅድሚያ የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት የሰብሉን ምርታማነት ለማሳደግ ጥረት መደረጉንም አስረድተዋል።
የዘማች ቤተሰቦች በመጪው በጋ የቤት እንስሳት የመኖ እጥረት እንዳያጋጥማቸውም በየወረዳው በተዘጋጁ መሬቶች ዘላቂ የመኖ እጸዋት እየለማ መሆኑን ያመለከቱት የግብርና መምሪያው ሃላፊ÷ነጻ ህክምና የሚያገኙበት አሰራር እየተመቻቸ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የዘማች ቤተሰቦቹ በዘንድሮ ክረምት የመኸር እርሻ ከዘሯቸው ሰብሎች መካከልም በቆሎ፣ ጤፍ፣ ዳጉሳ፣ ገብስ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾ፣ ሩዝ፣ ማሽላና ሰሊጥ ይገኙበታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

