አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 20 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሁለተኛው ምዕራፍ የሰቆጣ ቃል ኪዳን መርሃ ግብር ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ይፋ ሆነ።
በመርሃ ግብሩ ከሁሉም ክልሎች የተመረጡ 240 ወረዳዎች ላይ የመቀንጨር ችግርን ለማቃለል እንደሚሰራ ታውቋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፥ ኢትዮጵያ በመቀንጨር ችግር ሳቢያ በየአመቱ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እንደምታጣ ገልጸዋል።
ችግሩን ለመፍታት መንግስት ከአጋር አካላት ጋር የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው የሰቆጣን የቃል ኪዳን ስምምነት እንደ አብነት አንስተዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ የሰቆጣ ቃልኪዳን የማስፋፊያ ፕሮግራም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መቀንጨርን ለመቀነስ የተሰሩትን ስራዎችም አድንቀዋል።
“አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ አንዘነጋም” ያሉት ፕሬዚዳንቷ ሆኖም የሚከናወኑ ስራዎች በሙሉ በተሻለ ፍጥነትና ውጤታማነት ሊከወኑ ይገባል ብለዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው የመቀንጨር ችግር ለአገሪቷ ሁለንተናዊ ተፅዕእኖ የሚያሳድረውን ችግር በመገንዘብ የምግብና ስርዓተ ፖሊሲ ከመተግበር ባለፈ ሌሎች ስራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ 58 በመቶ የነበረውን የመቀንጨር ችግር ወደ 37 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የመቀንጨር ችግርን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ለ15 አመታት የሚያገለግል የሰቆጣ ቃል ኪዳን ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
በዚህ ሰነድ እስከ 2020 ዓ.ም ከ7 ሚሊዮን በላይ ከሁለት አመት በታች ያሉ ህጻናት እንዳይቀነጭሩ ለማድረግ ቃል ተገብቷል።
የሰቆጣ ቃልኪዳን የመጀመሪያ ምዕራፍ ከ2010 እስከ 2013 ዓ.ም ተከናውኖ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ባሉ 40 ወረዳዎች ሲተገበር ቆይቷል።
በመጀመሪያው የሙከራ ምዕራፍ ትግበራ ነፍሰጡርና ጡት የሚያጠቡ እናቶች እንዲሁም ከአምስት አመት በታች ያሉ ህጻናትን የጤና እና ስርዓት ምግብ ማረጋገጥ መቻሉ ተነግሯል።
በንጥረ ነገር የበለጸጉ ምግቦችና የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ማረጋገጥ የተቻለ መሆኑም ተነግሯል።
በሁለተኛው የማስፋፊያ ምዕራፍ ትግበራ እስከ 2020 ዓ.ም ከሁለት አመት በታች ያሉ ህጻናትን ከመቀንጨር ለመታደግ ይሰራል ተብሏል።
በመረሃ ግብሩ ማብሰሪያ ላይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የትምህርት ሚኒስቴርና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

