Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ ሕገወጥና የሌብነት ተግባርን ለሚያጋልጡ የማበረታቻ ስርዓት ተዘረጋ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 26፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)ተከማችቶ የቆየውን ሕገወጥ እና የሌብነት ተግባር ለማጥፋት በተደራጁ ሌቦች ላይ ተገቢው እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡

ሆኖም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከነዋሪው ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እና እነዚህ ህገወጥ ተግባር ፈጻሚ ሌቦችን የሚያጋልጥ የከተማው ነዋሪ ሊያበረታታ የሚያስችል የማበረታቻ ሥርዓት በመዘርጋት ሕገወጥነትን መከላከል አስፈላጊ በመሆኑ የከተማው ካቢኔ ባሳለፈው ውሳኔ “ሕገ-ወጥነትን ለሚጠቁሙ መረጃ አቅራቢዎች ስለሚሰጥ ማበረታቻ ደንብ” አውጥቷል፡፡

ደንቡ ከለያቸው ዋና ዋና ህገ-ወጥ ተግባራት ውስጥ የመሬት ወረራ፤ በመሬት ባንክ ተይዘው የነበሩ ይዞታዎችን ሕገወጥ በሆነ መንገድ የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንዲወጣባቸው ማድረግ፤ሕገ-ወጥ ግንባታ፤ የአርሶ አደር ይዞታዎችን በህገ ወጥ መንገድ ለማይገባው ሰው መብት እንዲፈጠር ማድረግ፤አላግባብ የመንግስት ቤቶችን፣ ሼዶችን፣ አረንጓዴ ቦታዎች እና ሌሎች ማንኛውም የመንግስት ይዞታዎችን ወደ ግለሰብ ማዞር ይገኙበታል፡፡

እንዲሁም በመሬት፣ በመሬት ነክ እና በማናቸውም የከተማው አስተዳደር አካላት ላይ የተመደበ ኃላፊ ወይም ሠራተኛ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የመንግስት አግልግሎቶችን በገንዘብ መሸጥ፣ ጉቦ እና መማለጃ መቀበል በግልጽ ባለቤት ሳይኖራቸው በህገ-ወጥ መንገድ ተገንብተው ያሉ ሕንጻዎች እና ታጥረው የተያዙ ባዶ ቦታዎችን ይዞ መገኘት፤ በስም ዝውውር መክፈል የሚገባውን የአሹራ፣ የቴምብር ቀረጥ፣ እና ሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎች ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ቀንሶ ማስከፍል ፡፡

በተጨማሪም መሠረታዊ የንግድ ዕቃዎችን በመደበኛ የንግድ መስመር እንዳይሸጥ መደበቅ፣ ማገድ ወይም መያዝ፤ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ በህገወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሬ ማዘዋወር፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ገንዘቦችን በማተምና በማሰራጨት የማጭበርበር ወይም የማታለል ተግባር መፈፀም፤ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት አገልግሎት መቀበልና መስጠት እና ሌሎች በወጣው ደንብ የተዘረዘሩ ናቸው፡፡

ማበረታቻውም ተጨባጭ መረጃ ያስገኘውን ውጤት መሠረት በማድረግ በገንዘብ የሚሰጥ ይሆናል ተብሏል፡፡

ጥቆማ ያለው ማንኛውም መረጃ አቅራቢም በነጻ የስልክ መስመር 9977 ፣በአካል ከንቲባ ጽ/ቤት 4ኛ ፎቅ በመምጣት፣ በኢሜል acity4338@gmail.com ላይ ጥቆማውን ማድረስ እንደሚችል ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስሴክሬቴሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version