አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ጉባኤው ያስተላለፈው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለመላው ኢትዮጵያዊያን በሙሉ እንኳን ከዘመን ዘመን በሰላምና በጤና አሸጋገራችሁ እያለ አዲሱ ዓመት 2014 ዓ.ም በሀገራችን በሁለንተናዊ መልኩ ፍጹም ሰላም እና አንድነት የምናይበት ስኬትን የምናስመዘግብበት እንዲሆን ጉባኤያችን ልባዊ ምኞቱን ይገልፃል፡፡
አዲሱን 2014 ዓ.ም ስንጀምር የጉባኤያችን የበላይ ጠባቂ አባቶች የጳጉሜን ወር በጸሎት አና ጾም እንዲያልፍ አዋጅ በማወጅ እና መልካም ምኞት በመግለጽ በሀገራችን የሚታዩ ግጭቶች፣ ያለመግባባቶች፣ በደሎችና ጉዳቶች በዘላቂነት ተፈትተው ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሰላምና በመከባበር መንፈስ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ሁሉም የሚጠበቅበትን ሊወጣ ይገባል፡፡
ለዚህም በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ፃገር ያሉ ኢትዮጵያውያን አማኖች ሁሉ የዕድሜ፣የጾታ፣ የማህበራዊ እና መሰል ሁኔታዎችን ሳይለዩ ስለሃገራቸው ሰላም እና አንድነት ስለወገኖቻቸው ሁለንተናዊ ደህንነት እንደሀገር ያጋጠሙንን ፈተና ለማለፍና መጪውን ዘመን ለሁላችንም የተሻለ እንዲሆን እያንዳንዳችን የሃይማኖታችን አስተምህሮና ሥርዓት በሚያዘው መሠረት ከአባቶቻቸን ጋር በመሆን ወደፈጣሪ አጥብቀን እንድንጸልይ ተቋሙ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ከዚህም ባለፈ ሃይማኖቶች የሰላም፣ የይቅርታ፣ የምህረት፣ የዕርቅ፣ የመተዛዘን እና የመረዳዳት ምሳሌዎችና መሰረቶች በመሆናቸው የሰው ልጅ በምድር ላይ ሲናር በጎውን እና መልካሙን እንዲሰሩ በማስተማር ማህበራዊ አንድነትን እና የሰውን በጎ ትስስር የሚያጠፉ የክፋት እና የጥላቻ አስተሳሰቦችን እና ተግባራትን እንዲያወግዙ በአጽንኦት ለማሳሰብ ይወዳል፡፡
በተጨማሪም ሁሉም አማኞች አዲሱን ዓመት ሲቀበሉ በተለያየ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉትን፣በጦርነት የተጎዱትን በማሰብና የሰብኣዊ ድጋፍ በማድረግ ሊሆን ይገባል፤ ይህም በሃይማኖቶች የተወደደ እና የተቀደሰ መልካም ተግባር መሆኑን ለማስታወስ እንወዳለን፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

