Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሶማሌ ክልል ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ፅህፈት ቤት 10 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት አስረከበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል መንግሥት ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ፅህፈት ቤት ለዱቄት እና ዳቦ ፋብሪካ ግንባታ የሚሆን 10 ሺህ ሄክታር መሬት አስረከበ።

በርክክቡ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መሀመድ ዩሱፍ÷ የቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ፋንታ፣ የጅግጅጋ ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ ሻፊ እንዲሁም ከሚድሮክ ኢትዮጵያ የመጡ ባለሙያዎች ተገኝተዋል ተብሏል፡፡

የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት በቅርቡ የዱቄት ፋብሪካ እና የዳቦ ፋብሪካ ለመገንባት ከመረጣቸው 10 ከተሞች ውስጥ የጅግጅጋ ከተማ አንዷ መሆኗ ይታወሳል፡፡

ለዚህም በ80 ሚሊየን ብር ወጪ በጅግጅጋ ከተማ ለሚገነባው ፋብሪካ 10 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ዛሬ ከጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር መረከቡን የክልሉ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዘግቧል፡፡

የምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መሀመድ ዩሱፍ እንደገለፁት÷ በቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ፅህት ቤት በጅግጅጋ ከተማ የሚገነባው ፋብሪካ በከተሞች ያለውን የኑሮ ውድነት እንደሚቀንስና በጅግጅጋና አከባቢው ለሚገኙ የስንዴ አምራች አርሶአደሮች የገበያ ትስስርን ይፈጥራል፡፡

ፋብሪካው ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥርና የቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ፅህፈት ቤት በጅግጅጋ ከዚህ በፊት ትምህርት ቤት መገንባታቸውንና ይህ ፋብሪካም ሁለተኛው ፕሮጀክት በመሆኑ በሶማሌ ክልል መንግሥት ስም ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።

የቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ፋንታ በበኩላቸው÷ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በሀገሪቱ 10 ከተሞች በ800 ሚልየን ብር ወጪ የሚገነባቸው ፋብሪካዎች የጅግጅጋው አንዱ ነው ብለዋ፡፡

ፋብሪካው ተገንብቶ ሲጠናቀቅም በቀን 420 ሺህ ኩንታል ስንዴና እና 300 ሺህ ዳቦ የማምረት አቅም ይኖረዋል ብለዋል።

የፋብሪካው ግንባታም በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

የጅግጅጋ ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ ሻፊ አህመድ እንደተናገሩት÷ በጅግጅጋ ከተማ ከ700 ሺህ ህዝብ በላይ እንደሚኖር ገልፀው÷ ለህዝቡ ዳቦ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርብ ፋብሪካ የቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ፅህፈት ቤት በጅግጅጋ ላይ ለመገንባት ከተማዋን በመምረጣቸው ምስጋና አለኝ ብለዋል።

በዚህም የከተማ አስተዳደሩ በዛሬው እለት 10 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ እንዳስረከበ ተናግረዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version