አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በነገው አሰለት የሚከበረው የመሰቀል ደመራ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ተከብሮ ይውል ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉን አቀፍ ትብብር እና ድጋፍ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥሪ አቀረበች።
የሰላም፣የአንድነት፣የፍቅርና የስምምነት መገለጫ የሆነው የመስቀል ደመራ በዓል በነገው እለት በመላ ኢትዮጵያ ተከብሮ የሚውል ሲሆን በዓላችንን በሰላምና በደስታ ማክበር እንችል ዘንድ ከጸጥታ ማስከበር ጋር ተያይዞ በመንግሥት የጸጥታ አካላት የሚተላለፉ መልዕክቶችን መከታተልና መተግበር እንደሚገባ ቤተክርስቲያኒቱ ገልጻለች።
በተለይም ወደ መስቀል አደባባይ የሚጓዙ ምዕመናን የጸጥታ አካላት ለሚያደርጉት ፍተሻ ፍጹም ተባባሪ በመሆን ግብረ ሽበራን መከላከልና አጠራጣሪ የሆኑ ምልክቶችንም ሲያጋጥመው ለጸጥታ አካላት በመጠቆም በዓላችንን ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር ማክበር እንችል ዘንድ ክርስቲያናዊ ጨዋነትን የተላበሰ ትብብርና ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቃል ስትልም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥሪዋን አቅርባለች።
በበዓሉ ወቅት በሚደረጉ ትርኢቶች ፣መንፈሳዊ ዝግጅቶችና በዓሉን ለማክበር በመስቀል አደባባይ የሚገኙ ምዕመናን ሁሉ እኛ ኦርቶዶክሳዊያን ሕግና ሥርዓት አክባሪዎች መሆናችንን በሚያስመሰክር መልኩ ሕጋዊውንና በህገ መንግሥቱ የጸደቀውን ሰንደቅ አላማ ወይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አርማ ያለበት ያልተጣጣፈና በግልጽ ከፊትም ከኋላም የሚታይ ባንዲራ ብቻ ይዞ መውጣትና ከዚህ ውጪ ያሉ ማንኛቸውንም አርማና ባንዲራዎችን ባለመያዝ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንደሚገባ ቤተክርስቲያናችን ለማሳሰብ ትወዳለችም ተብሏል።
በዓሉ በምልዓተ ሕዝብ የሚከበር በዓል ከመሆኑ አንጻርም ሁሉንም የኮቪድ 19 የቅድመ ጥንቃቄ መርሆችን በማክበርና በመፈጸምም የራሳችንንና የወገኖቻችንን ህይወት መጠበቅ እንደሚገባንም ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በበዓሉ ወቅት በመስቀል አደባባይ የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኮቪድ 19 ምርመራና ክትባት የሚሰጥ መሆኑን አውቃችሁ ምርመራ በማድረግና ክትባት በመከተብ የበሽታውን ሥርጭት በጋራ አንድንከላከል በሚኒስቴር መስሪያቤቱ አማካኝነት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን በዚህ አጋጣሚ ለመጠቆም እንወዳለን።
“ልዑል እግዚአብሔር በዓላችንን የሰላም ፣የደስታ ፣የፍቅር ፣የአንድነትና የስምምነት ያድርግልን።” ስትል ቤተክርስቲያኒቱ ጥሪ አስተላልፋለች።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

0
People Reached
0
Engagements
Boost Post
Like
Comment
Share