አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2014 (ኤ ቢ ሲ) የመስቀል በዓልን ስናከብር ግዛታዊ አንድነታችንን ለማስጠበቅ በዱር በገደል የሚዋደቁ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን በማሰብ መሆኑን የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ ገለፁ፡፡
ከንቲባው ይህን ያሉት ዛሬ የመስቀል በዓል በጎንደር ከተማ በተከበረበት ወቅት ነው፡፡
በአሸባሪው ህውሓት ቡድን በግፍ የተፈፀመብንን ወረራ ለመመከትና ሀገርን ከጥፋት ለመታደግ በሚደረግ የህልውና ዘመቻ ውስጥ ማክበራችን የዘንድሮውን የመስቀል በዓል የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።
የመስቀልን በዓል ስናከብር የመስቀሉን ፍኖት ተከትለው ግዛታዊ አንድነታችንን ለማስጠበቅ በዱር በገደል የሚዋደቁ እህቶቻችንና ወንድሞቻችንን በማሰብ ሊሆን እንደሚገባም ነው ከንቲባው የገለጹት፡፡
እነርሱ እንደ ደመራ አንድ ሆነው ለኢትዮጵያ የሚሰው ህያዋን ችቦዎች ናቸው ያሉት ከንቲባው÷ በተመሳሳይ በወራሪው ቡድን የተጎዱ ዜጎችን አለሁ ልንላቸው ከጎናቸውም ልንቆምም ይገባል ብለዋል፡፡
ከቤት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችን መልሶ የማቋቋም፣ የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን የመገንባትና የወደሙ የጤና ተቋማትን በምትካቸው የመስራት ግዴታ የሁላችን ነውም ብለዋል፡፡
አሁን አገልግሎት የሚሰጠውን የመስቀል አደባባይ በዘመናዊ መልክ ማስፋፋት የሚያስችል የዲዛይን ስራ በቅርቡ ተጠናቆ ይፋ እንደሚደረግ ከንቲባ ሞላ ተናግረዋል።
በመስቀል በዓሉ ለይ የተገኙት የማዕከላዊና የምዕራብ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ÷ ከመቼውም ጊዜ በላይ የእግዚአብሔር ዕርዳታ ለኢትዮጵያውያን እየደረሰ ነው ብለዋል፡፡
ይህን ያሉት ዛሬ በተከበረው የመስቀል በዓል ላይ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ነው።
ብፁዕነታቸው የኢትዮጵያ ጠላቶች ብዙ ቢሆኑም ኢትዮጵያ በፈጣሪ ዕርዳታ አሽናፊ ሁና ትቀጥላለች ብለዋል።
አሁን ጊዜው መረዳዳት እና መተባበር የሚጠይቅበት ትክክለኛው ወቅት መሆኑን ያነሱት አቡነ ዮሐንስ÷ በችግር ውስጥ የወደቁ ወገኖችን በፍጥነት ልንደርስላቸው ይገባል ብለዋ፡፡
በክርስቶስ መስቀል የተሰበከውን ፍቅር በማሰብ ምዕመናን ለሀገር ሰላም መሆኑን ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ነው ያሳሰቡት፡፡
የመስቀል በዓል በጎንደር ከተማ በተሳካ ሁኔታ ተከብሮ እንዲያልፍ በየተለያየ መንገድ ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በምናለ አየነው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!