አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መስቀል የሰው ልጆች ሁሉ የፍቅር ተምሳሌት በመሆኑ ሁላችንም ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለፍቅር መዘጋጀት አለብን ሲሉ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጠቅላይ ፀሃፊ አባ ተስፋዬ ወልደማርያም ተናገሩ፡፡
የመስቀል ደመራ የቤተክርስትያኗ ካህናት፣ አባቶችና የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት ችቦ በማብራት፣ በፀሎት፣ በቅዳሴ፣ እንዲሁም በሌሎችም መንፈሳዊ ስነ ስርዓቶች ተከብሯል።
በክብረ በዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በቤተክርስትያኗ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጠቅላይ ፀሃፊ አባ ተስፋዬ ወልደማሪያም÷ መስቀል የሰው ልጆች ሁሉ የፍቅር ተምሳሌት በመሆኑ ሁላችንም ለሰላም፣ አብሮነትና ፍቅር መዘጋጀት አለብን ብለዋል።
አንድነት፣ ህብረትና ሰላም ከተረጋገጠ ለዓለም ስጋት የሚሆኑ ነገሮች ሁሉ ቦታ አይኖራቸውም ሲሉም ተናግረዋል።
ለአንድነት፣ ለእርቅና ለሰላም ሲል ክርስቶስ መስቀል ላይ እንደተሰቀለ ሁሉ የሰው ልጆችም ለሰላም፣ ፍቅር እና አንድነት ሲሉ መልካም ተግባራትን ለመፈፀም መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።
በሃገራችን በአሁኑ ወቅት ህፃናት፣ ሴቶች፣ አቅመ ደካሞች የመፈናቀልና ሌሎችም ችግሮች እየገጠማቸው በመሆኑ ልናግዛቸውና ልንረዳቸው ይገባል ነው ያሉት።
አሁን ለገጠሙን ችግሮች ሁሉ መፍትሄ እንዲመጣ ምዕመኑ በትጋት መፀለይ አለበት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ምእመናን መስቀልን ሲያከብሩ ችግረኞችን በማገዝ በፍቅር፣ በሰላምና በመተሳሰብ መሆን እንዳለበት ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

