Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በግጭት ውስጥ መኖርን ህልውናው ያደረገው አሸባሪው ህወሃት የጦርነት ነጋሪት መጎሰሙን እንደቀጠለ ነው- ምንጮች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በግጭት ውስጥ መኖርን ህልውናው ያደረገው አሸባሪው ህወሃት የጦርነት ነጋሪት መጎሰሙን መቀጠሉን የሚያሳይ ቪዲዮ ከሰሞኑ ወጥቷል።

የአሸባሪው ቡድን ታጣቂ አመራር እንደሆኑ የሚነገርላቸው ግለሰቦች በሰጡት መግለጫ፥ቡድኑ አሁንም ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ እንድትቆይ የሚያደርግ ዝግጅት እንዳላቸው በይፋ ተናግረዋል።

“እያደረግን ያለነው ዝግጅት ዘመን ተሸጋሪ ዝግጅት ነው” ያሉት ግለሰቦቹ ፥ ወታደራዊ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ቡድኑ ህጻናትን ለጦርነት በማሰማራት ከሞራልና ከህዝብ ተቆርቋሪነት በራቀ መንፈስ አሁንም ቀውስ ውስጥ የመቆየት ፍላጎታቸውን በይፋ አውጥተዋል።

አሸባሪው ቡድን ህጻናትን ለጦርነት መማገዱ፣ ህዝብን ለከፋ ችግር መዳረጉና ለሚያካሂደው የሽብር ተግባር ህዝብ ድጋፍ እንዲያደርግ ማስገደዱ ተቀባይነት እያሳጣው መሆኑ ግልጽ እየወጣ መምጣቱን ምንጮች መግለጽ ጀምረዋል።

በዚህ የተነሳም ቡድኑ ከገባበት የሽብር ድርጊት እንዲወጣ በሚፈልጉና ሽብሩን ማስቀጠል በሚፈልጉ የአሸባሪው ህወሓት አመራሮች መካከል እስከ መገዳደል የደረሰ አለመግባባት ተፈጥሯል።

የግለሰቦቹ መግለጫም ከዚህ ምስጢር መውጣት ጋር የተገናኘ እንደሆነ ተገልጿል።

መግለጫውን የሰጡት ሰዎች የደረሰባቸውን ሽንፈት ለመሸፈን “በፖለቲካም፣ በህግም፣ በህዝባችን ሞራልም፣ በአለም ዲፕሎማሲም ብዙ ርቀት ሄደናል፣ በወታደረዊ አቅምም በተሻለ ደረጃ ላይ ደርሰናል” ሲሉ የሐሰት ፕሮፓጋንዳቸውን አሰራጭተዋል።

የአሸባሪው ቡድን አባላት ላይ ያነጣጠረውን የኢትዮጵያ መንግስት የህልውና ዘመቻ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ለማስመሰልም “የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ቢፈረድበትም ባካሄደው መራር ትግል አንድ ታላቅ ምእራፍ ተሸጋግሯል” ሲሉ ህዝቡን በመደለል ለመስዋዕትነት እያዘጋጁት እንደሆነ ግልጽ አድርገዋል።

የአሸባሪው ቡድን አመራሮች ጨፍጫፊውን ህወሓት “ለትግራይ ህዝብ መስዋዕትነት የከፈለ ነው” በማለት ህዝቡን ለረጅም ግዜ በስሙ በመነገድ ያደረሰበትን ግፍና ሰቆቃ በመሸፋፈን ለማጭበርበር ቢሞክሩም በመቀሌና የተለያዩ የትግራይ አካባቢ የሚኖረው ህዝብ፣ የህወሓትን የሽብር ቡድን እስከ ሰልፍ በደረሰ ተቃውሞ ለቡድኑ ያለውን ጥላቻ እየገለፀ፣ በዚህም ሳቢያ በሽብር ቡድኑ ግድያ እየተፈፀመበት መሆኑን ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

Exit mobile version