አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ቡድን ሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን በምሽግነት ለመጠቀምና ለማውደም ያደረገው ሙከራ በማኅበረሰቡና በጸጥታ ኃይሉ መክሸፉን የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።
“ቱሪዝም ለሁለንተናዊ እድገት” በሚል መሪ ቃል የቱሪስት መዳረሻ የሆኑትን ቅርሶች ከጠላት መጠበቅና አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ከሚያደርሰው ጥፋት ለመታደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የከተማው ነዋሪዎች መክረዋል፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ ተሳትፎና አደረጃጀት አማካሪ አቶ ወገኔ አማረ አሸባሪው ቡድን ሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን በምሽግነት ለመጠቀምና ለማውደም ያደረገው ሙከራ በማኅበረሰቡና በጸጥታ ኃይሉ የተቀናጀ ሥራ ቅርሱን መታደግ እንደተቻለ አብራርተዋል፡፡
የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው የሰሜን ጎንደር ማኅበረሰብ ኑሮው የተመሰረተው በቱሪዝም ላይ በመሆኑ ሊጠብቀውና ሊንከባከበው እንደሚገባ ነው ያብራሩት፡፡
አሁን ላይ ያሉ ፈተናዎች ማለፋቸው የማይቀር ነው ያሉት አቶ አበባው፥ የቱሪስት መስህቦችን በመጠበቅና በመንከባከብ ከቱሪስት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የነበሩ ክፍተቶችን በመገምገምና በማረም በቀጣይ ወደዞኑ የሚመጣውን ጎብኚ ለማስደሰት አካባቢውን በሁሉም ዘርፍ ምቹና የተሟላ አድርጎ ማዘጋጀት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ እንደተነገረው፥ ሰሜን ጎንደር ዞን አንዱ እንደመሆኑ በኮረና ወረርሽኝ ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረውን የዞኑን የጎብኝዎች ፍሰት፥ አሸባሪው የትህነግ ቡድን የፈጸመው የወረራ ጦርነት ሙሉ በሙሉ እንዲቆም አድርጎታል፡፡
የደባርቅ ከተማ ባለሀብት የሆኑት አቶ መኳንንት ደሳለኝ ፥ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በዞኑ የከፈተው የወረራ ጦርነት በገቢያቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
የሰሜን ተራራች ብሔራዊ ፓርክ የግል አስጎብኚ ማኅበር አባል የሆነው ወጣት ታደለ ሞላ፥ በደባርቅና ዳባት ያልተሳካለት አሸባሪው ትህነግ፥ በፓርኩ ላይ ጥቃት ለመፈጸም እየሞከረ በመሆኑ ለሀገሪቱ የገቢ ምንጭ፤ ለዞኑ ማኅበረሰብ የህልውና መሰረት የሆኑትን የቱሪስት መስህቦች ከጠላት የመጠበቁ ተግባር ሊጠናከር እንደሚገባ ማሳሰባቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዮሐንስ ባዬ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ቦታዎችን በማጥናትና ታሪካዊ ቅርሶችን በመጠበቅ ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ለማድረግ እንደሚጥር ነው ያረጋገጡት፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!