Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢሬቻ በዓል በሰላም አንዲከበር ዝግጅት ተጠናቋል-ፖሊስ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲካሄድ ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በጋራ ወደ ሥራ መግባቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በዚሁ መሠረት በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከሀገር መከላከያ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከፌዴራል፣ ከኦሮሚያና ከአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ እንዲሁም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጣ ልዩ ልዩ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱም ተገልጿል፡፡
አባገዳዎች፣ አደ ስንቄዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል መስከረም 22 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይከበራል፡፡
ለዚህም በዓሉ በሰላም እንዲከበር መላው የፀጥታ አካላት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የኢሬቻ ሆራ ፊንፍኔ በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታ አካላት ለወንጀል መከላከል ተግባራቸው ልዩ ትኩረት በመስጠት አብዛኛውን የሰው ኃይላቸውን በወንጀል መከላል ስራ ላይ ማሰማራታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅሶ በተለይ በዓሉ ወደ እሚከበርበት ስፍራ የሚመጡ ታዳሚዎች ለጋራ ደህንነት ሲባል ፍተሻ መኖሩን ተገንዘበው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡
ከዚህ ቀደም የተከበሩ ሃይማኖታዊና ብሄራዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር ወሳኝ ስራ ማከናወኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውሶ የዘንድሮው የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል በሰላም እንዲከበር የበዓሉ ታዳሚዎች እና የከተማው ነዋሪ የተለመደውን ትብብር እንዲያደርጉ በፀጥታ አካለት ስም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በመጨረሻም ህብረተሰቡ የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘትም ሆነ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት መረጃ ለመስጠት በ991 ወይም 816 ነፃ የስልክ መስመሮችን እና 01- 11 -11- 01 -11፣ 01- 11- 26- 43- 59፣ 01- 11- 01- 02- 97፣ መጠቀም እንደሚቻል አስታውቆ÷ ለፀጥታው ስራ ስኬታማነት ህብረተሰቡ እያደረገ ላለው ቀና ትብብር በመላው የፀጥታ አካላት ስም ምስጋናውን እያቀረበ በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version