አዲስ አበባ፣መስከረም 21፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በሀገራዊ የመንግስት ምስረታና በኢሬቻ በዓል መርሃ ግብሮች ላይ የፀጥታና ደህንነት ዝግጁነት ላይ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የአገር መከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን እና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ተቋማት ሥራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
የፀጥታ ሀይሉ የደረሰበትን የዝግጁነት ደረጃ እንዲሁም በተግባር በቴክኖሎጂ የተደገፉ ዝግጁነቶች ላይም ምክክር ተደርጓል።
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ÷”የመረጃና ደህንነት ስራ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን የጋራ ስራ ነው” ብለዋል።
ከለውጡ በኋላ የፀጥታ ተቋማቱ በጋራ መስራት እንደጀመሩ ገልፀው፤ በዚህም በርካታ በዓላትን በሰላምና በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉን ተናግረዋል።
በቀጣይ ቀናት የሚካሄዱ አገራዊ የመንግስት ምስረታ እና የኢሬቻ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲካሄድ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አስፈላጊ ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በበኩላቸው ÷ በሳይበር ጥቃት ማድረስ የሚፈልጉ ሀይሎች ቢኖሩም ይሄንን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ዝግጅቱን በተመለከተ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ሲሳይ ቶላ በሰጡት ማብራሪያ÷ ከአዲስ መንግስት ምስረታ እና ከኢሬቻ በዓል ጋር ተያይዞ ያሉ ወቅታዊ ስጋቶችን ተንትነዋል።
የአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ፣ አልሸባብና አይ.ኤስ.አይ.ኤስ እንዲሁም ሌሎች የአዲስ መንግስት ምስረታውን እና የኤሬቻን በዓል ለማወክ ወቅታዊ ስጋት መሆናቸውን አብራርተዋል።
በዚህም በተለይም በዓለ ሲመቱ ላይ ያነጣጠረ የሽብር ጥቃት ለማካሄድ ፍላጎት መኖር፣ በግንባር ደግሞ ግጭት በመክፈት ወቅታዊ ሁኔታውን ለማደብዘዝ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚሉ የስጋት ትንታኔዎችን አቅርበዋል።
በተጨማሪም “በታዋቂ ሰዎች ላይ ሊቃጣ የሚችል የግድያ ሙከራዎች እና ቁልፍ የመሰረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ታሳቢ ያደረገ ሙከራዎችን ጠላት ሊያደርግ ይችላል” የሚል ግምገማ የያዙ ዝግጅቶች መደረጉን ተናግረዋል።
እነዚህን ስጋቶችን ለመቀልበስ በብሄራዊ ደረጃ የተደራጀው የፀጥታ አስተባባሪ ኮሚቴ በተለያዩ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ቴክኖሎጂዎች በምድርም በሰማይም እንደሚጠቀም አመልክተው፤ በተለይ እንደ ድሮንና ሲ.ሲ.ቲቪ የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎችን በመታገዝ የክትትል አቅምን የማሳደግ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል÷ መንግስት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በሰራው የሪፎርም ስራ “ከዚህ በፊት በጋራ ተገናኝተው ሰርተው የማያውቁ ተቋማት በጋራ ለአገር እየሰሩ ነው” ብለዋል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ ÷አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ “በአገርና ህዝብ ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት አስቀድሞ ለመከላከል ገቢራዊ የተደረገው ቴክኖሎጂ እገዛ ያደርጋል” ብለዋል።
የአገር መከላከያ ተወካይ ብርጋዴር ጄነራል አብድሮ ከድር በበኩላቸው÷አሁን የተከናወኑት ተግባራት “በጸጥታና ደህንነት ሥራዎች ያለውን አቅም ያሳያል” ብለዋል።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋሸና በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የፀጥታ ሃይሉ የሚጠቀምበት ቴክኖሎጂ “አመራሩ በቴክኖሎጂ በቀጥታ እየተመለከተ ስምሪት መስጠት እንዲችል ማድረጉ ትልቅ እመርታ ነው” ብለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው÷ የሚሰማራውን የሰው ሀይል ቁጥር ከማብዛት ይልቅ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ስራዎችን ማከናወኑ ጊዜና ጉልበት በአግባቡ ከመጠቀም ባሻገር ፍጥነትና ቅልጥፍናን ለመጨመር ያስችላል ተብሏል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!