አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሎጀስቲክስ ካዉንስል በባህር ተጓጉዘው ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ዕቃዎች ትራንስፖርት የሚከፈለውን የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም ለማሻሻል የተዘጋጀውን የፍሪ ኦን ቦርድ (ኤፍ ኦ ቢ) መመሪያ ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
የፍሪ ኦን ቦርድ (ኤፍ ኦ ቢ) አሰራር ገቢ ዕቃን በማሰባሰብ ዝቅተኛ የባህር ትራንስፖርት ዋጋ ለማስገኘትና የውጭ ምንዛሪ ብክነትን ለመከላከል የሚያስችል ሲሆን÷ በሂደቱም የሃገር ውስጥ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎችን አቅም አጠናክሮ ሀገራዊ ፖሊሲን ለመተግበር የተሻለ ዕድል ይሰጣል ተብሏል፡፡
የመመሪያው መጽደቅ በመልቲሞዳል ሎጂስቲክስ ኦፕሬሽን ላይ የነበረውን ሞኖፖሊ በማስቀረት ቀስ በቀስ ወደነጻ የገበያ ውድድር ለማሸጋገር እንዲቻል አምስት የመልቲሞዳል ኦፕሬተሮች በዘርፉ እንዲሳተፉ የሚፈቅደውን እና በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. የጸደቀውን የመልቲሞዳል ኦፕሬሽን መመሪያ ቁጥር 802/2013 ተግባራዊ እንዲሆን ያስችላል፡፡
የመልቲሞዳል ኦፕሬሽን ለግሉ ዘርፍ ክፍት መሆን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት የፈጠረውን ከፍተኛ የወጪ ገቢ ጭነት ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ፍላጎትን ለማስተናገድ ዕድል የሚፈጥር ነው ተብሏል፡፡
በገበያ ውድድር ከሚገኝ የዝቅተኛ ዋጋ አማራጭ እና የአገልግሎት ውጤታማነት ሃገሪቱን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልጿል፡፡
የፍሪ ኦን ቦርድ (ኤፍ ኦ ቢ) መመሪያ መጽደቅን ጨምሮ በብሔራዊ ሎጂስቲክስ ስትራቴጂው ተለይተው በዘርፉ እየተከናወኑ የሚገኙ የለውጥ ሥራዎች መተግበር የሎጂስቲክስ ሥርዓት ላይ ውጤታማነትን በመጨመር ከዓለም አቀፍ ሎጂስቲክስ አፈጻጸም ቀመር አንጻር የኢትዮጵያን ደረጃ ከፍ ለማድረግ ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል መባሉን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን