አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)በኢትዮጵያ ምድር በአመፅና በጠመንጃ ትግል ወይም ንፁሃንን በማሻበር የሚገኝ ስልጣን ከእንግዲህ እንደማይኖር ሊታወቅ ይገባል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጋራ መክፈቻ ጉባኤ የተካሄደ ሲሆን ÷በሁለቱም ምክር ቤቶች የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ንግግር አድርገዋል፡፡
በንግግራቸው አዲስ ለተመረጡት ጠቅላይ ሚኒስትር፣የህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔና ምክትል አፈ ጉባኤ መልካም ምኞታቸውን ገልፀው÷ አምስት ዓመት የሚቆየው የእነዚህ ምክር ቤቶች መከፈት በየዓመቱ ከሚደረጉ መክፈቻ ስነ ስርዓቶች ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው ያሉ ሲሆን ይህም የአንድ ን ምዕራፍ መጠናቀቅ እና የአዲስ የተስፋ ምዕራፍ መከፈት ነው ብለዋል፡፡
በንግግራቸው ባለፉት ዓመታት አብሮ መኖራችንን ለማናጋት ብዙ ተሰርቷል ብዙ ዋጋም ተከፍሏል፤የዛ ትግልና ፅናት ድምር ደግሞ ለዛሬ አዲስ ምዕራፍ አብቅቶናል ፤ለዚህ ምዕራፍ ያበቁንን ዋጋ የከፈሉትን ሁሉንም ደግሞ ማስታወስ ተገቢ ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡
በ2013 የተካሄደው ምርጫ በበርካታ መለኪያዎች ካለፉት ዓመታት ሻለ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ ባለፉት ሶስት ዓመት ሲወሰድ የነበረው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ኢኮኖሚው ከነበረበት የቁልቁለት ጉዞ በመታደግ ከፍተኛ ውጤት አምጥቷል፤ ከሞላ ጎደልም ውጤታማ ነበሩ ብለዋል፡፡
ነገር ግን የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት የኢኮኖሚው ፈተናዎች ሆነው ቀጥለዋል፡፡
ያለፈው አመት የህዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት የተከናወነበት እንዲሁም ሌሎች ስኬቶች የተገኙበት አመት ነበር ያሉት ፕሬዚዳንቷ ዓመታቶቹ እንደ ሃገር ታላላቅ ስኬቶች ያስመዘገብንበት ቢሆንም አሳዛኝ ድርጊቶችም የተፈፅመዋል ነው ያሉት፡፡
በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ከሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎች ጋርም በንጹሀን ላይ ግድያ ፈፅመዋል፣ ንብረት ወድሟል፣መፈናቀል ሲፈጽሙ ቆይተዋል፤ በዚህም አሁን ህብረተሰቡ ወደ ቤት ንብረቱ እንዲመለስ እና በቶሎ እንዲያገግም ማድረግ ተጠናክሮ የሚቀጥሉ ጉዳዮች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
በሌላ በኩልም በ2014 በጀት ዓመት የመንግስት ገቢን 600 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ለማድረግ ታቅዷል ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 83 በመቶ የሚሆነውን ከታክስ ለመሰብሰብ መታቀዱን አመላክተዋል፡፡
ጠቅላላ የሸቀጦች የውጭ ንግድ ገቢን ደግሞ 5 ነጥብ 25 ቢሊየን ዶላር ለማድረግ ታቅዷል፡፡
እንዲሁም በተያዘው በጀት ዓመት የውጭ ንግድና የውጭ ምንዛሬን እንዲያድግ ይሰራል፤በከተሞች ባልተማከለ የከተማ አስተዳደር እንዲኖር ደረጋል ብለዋል፡፡
ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኝን ገቢ ለማሳደግም ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎች ይጎለብታሉ፤ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲለሙ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ይሆናሉ ነው ያሉት፡፡
በአመፅና በጠመንጃ ትግል ወይም ንፁሃንን በማሻገር የሚገኝ ስልጣን ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር እንደማይኖር ሊታወቅ ይገባል ሲሉ አፅንኦት የሰጡት ፕሬዚዳንቷ ፤ስልጣን ሰጪውም ስልጣን ነሺውም የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችም በህጋዊ ምርጫ ላይ ብቻ በመሳተፍ ህዝባችሁን የምታገለገሉበት ሰላማዊ መንገድ እንድትከተሉ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በደም የተፃፈን ታሪክ ብዕር ቀለም አይለውጠውም ያሉት ፕሬዚዳንቷ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ብሄራዊ ጥቅምና ልኡላዊነት ከማንም ጋር አንደራደርም ብለዋል ፡፡
ለዚህም የውጭ ግንኙነት መርህ የኢትጵያን ልዑላዊነት የሚያከብር፣ብሄራዊ ጥቅማችንን እና ክብራችን በማያጓድል መልኩ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ለቀጣይ ጎረቤት አገራትን ያስቀደመ የዉጭ ግንኙነት ፖሊሲ ቀርፀን እንሠራለን ነዉ ያሉት ፕሬዚዳንቷ፡፡
በምሥራቅ አፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ብዙ ፍላጎቶች የሚንፀባረቁ መሆኑን በመግለጽም፣ ኢትዮጵያ በቀጣናዋ የሚፈፀሙ ገዳዮችን ከሩቅ ሆና አትመለከትም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ትሥሥር እና የጋራ ብልጽግናን መሠረት ያደረገ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም በዙሪያችን ያሉ ጎረቤት ሀገራትን ያስቀደመ ሆኖ እንደሚቀጥል እና በትብብር እና በመግባባት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚተገበር እንደሚሆንም አብራርተዋል።
በፌቨን ቢሻው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!