Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሚኒስትሮቹ ሹመት የበለጸገች ሃገርን ለመገንባት መሰረት የጣለ ነው-የደብረ ብርሃን ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፣መስከረም 26፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተሰየመው አዲሱ የአስፈጻሚ አካላት ሹመት የበለጸገች የጋራ አገር ለመገንባት መሰረት ጥሏል ይላሉ የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች፡፡
ነዋሪዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንዳመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስፀደቁት ሹመት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር መስፋቱን ያመለክታል።
በዚህም በህወሃት ዘመነ ሥልጣን ከአገር ሲባረሩና እንግልት ሲደርስባቸው የቆዩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥልጣን በመጋራት አገር ለመምራት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ አቶ ይንገሱ ግርማ የሚኒስትሮች ሹመት ለቀጣይ የሀገራዊ ግንባታ መሰረት ጥሏል ይላሉ።
በተለይ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተሿሚዎች ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ለሕዝባቸውና ለአገራቸው እንዲያበረክቱ ዕድል ሰጥቷል ሲሉም ያክላሉ።
በቀደሙት ጊዜያት ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ባላቸው ተቆርቋሪነት ብቻ ተነጥለው የሚሳደዱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የእንግልት ታሪክ ምዕራፍ መዘጋቱንም ይናገራሉ።
ሌላው የከተማው ነዋሪ መሪጌታ ምትኬ ቦጋለ በበኩላቸው ሹመቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የመደመር እሳቤ ተጨባጭ ማሳያ ነው ብለውታል።
በኢትዮጵያ ያለፉት ሦስት ዓመታት ለውጥ ወደ ተሻለ የልማትና የብልፅግና ጎዳና ለማሸጋገር እንደሚያስችል እምነታቸውን ገልጸዋል።
“ተሿሚዎች አገሪቱ የገጠሟትን ችግሮች ለመፍታት በተሰጣቸው ሃላፊነት በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።
ሹመቱ በትምህርት ዝግጅት፣ በልምድና በአገልጋይነት መንፈስ ከመስርት ባለፈ አንድነትን ያጠናክራል ያሉት ደግሞ አቶ ዓለሜ በላይ የተባሉት ሌላኛው የከተማው ነዋሪ ናቸው፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለመተግበርና የጋራ አገር ለመገንባት እንደሚረዳም ገልጸው ተሿሚዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ልዩ ስብሰባው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ 22 ሚኒስትሮችን ሹመት አጽድቋል።
ከተሻሚዎቹ መካከል የትምህርት፣የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የባህልና ስፖርት ሚኒስትሮች ላይ የተሾሙት የተፎካካሪ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች ሆነዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version