አዲስ አበባ፣ መስከረም 27 ፣ 2014 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች ሁለንተናዊ ትስስርን በማጠናከር የህዝቡን መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ትርጉም ባለው መንገድ ለመመለስ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የተጎራባች ክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች አስታወቁ።
ርዕሳነ -መስተዳድሮቹ በተገኙበት በምስራቅ ሐረርጌ የባቢሌ ወረዳ የኢፋ ቦሩ ዋዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
በወቅቱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ፥የሚቀጥሉትን 5 ዓመታት እንደ ሃያ ዓመታት በመስራት የህዝብን መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንመልሳለን ብለዋል።
በተለይ የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች ያላቸውን ሁለንተናዊ ትስስር በማጎልበት እና በተቀናጀ አግባብ የህዝብ ጥያቄዎች ለመመለስ የተጀመሩ ተግባራት እንደሚጠናከሩ ገልጸዋል።
የሚፈለገው ለውጥ እንዲመዘገብ ህብረተሰቡ የግብርና ምርቱን በዘመናዊ መንገድ ከማረስ ጎን ለጎን ተተኪው ወጣት ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኝና በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ክልሉ እንደ ባቢሌ ወረዳ ሁሉ በክልሉ ዞኖች የጀመራቸው የትምህርት ፕሮጀክቶች ዳር ይደርሳሉ ብለዋል።
የተጀመሩ የለውጥ ተግባራቱ በሚፈለገው ፍጥነትና ጥራት እንዲጓዙ ህብረተሰቡ በየአካባቢው ጠንካራ ስርዓት እንዲዘረጋ በማድረግ ከመንግስት ጎን በመሆን ተሳትፎውን እንዲያጠናክር መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሱማሌ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ በበኩላቸው ፥ ለውጡን ተከትሎ በኦሮሚያም ሆነ በሱማሌ ክልሎች የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ የሰላምና የልማት ተግባራት ይበልጥ በውጤት እንዲታጀቡ የሚደረገው ርብርብ ይጠናከራል ብለዋል።
በአሸባሪው ህወሓት ቡድን ሴራ በሁለቱ ክልሎች ህዝቦች መካከል የተሸረበው ተንኮል በለውጡ መንግስት ተበጣጥሶ የህዝብን ሁለንተናዊ ትስስርና በጋራ የማደግ ሂደት ፀንቶ መቀጠሉን አስታውቀዋል።
ለውጡን ተከትሎ የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች ተቀናጅተው በመተባበር ፣መደጋገፍና መረዳዳት ትርጉም ያለው የልማትና የመልካም አስተዳደር ውጤቶች በቁርጠኝነት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ነው የገለጹት።
በምስራቅ ተጎራባች ክልሎች ቅንጅት እየተመዘገቡ የሚገኙት የሰላምና የልማት ስራዎች የሚጠናከሩ ይሆናሉ ያሉት ደግሞ የሐረሪ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ናቸው።
ተጎራባች ክልሎቹ በጋራ ለመልማት እና የህዝብን የነቃ ተሳትፎ ለማጠናከር የባህል የታሪክ የማንነትና በጋራ ተሳስሮ የመኖር ጠንካራ እሴት ያላቸው መሆናቸውን አብራርተዋል።
በምስራቅ ሐረርጌ ባቢሌ ወረዳ ከ36 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባው የኢፋ ቦሩ ዋዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተመረቀበት በስነ-ስርዓት የጨፌው አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱርአህማን፣ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የአካባቢው ነዋሪዎች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

0
People Reached
0
Engagements
Boost Post
Like
Comment
Share