አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በአቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራው ልዑክ በአደአ ወረዳ የተዘራውን ኩታ ገጠም የጤፍ ማሳ ጎበኙ።
የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የኩታ ገጠም እርሻ ውጤት ማሳየት ጀምሯል ብለዋል ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ሽመልስ አብዲሳ።
በወረዳው በስፋት እየተሰራበት ያለው የክላስተር እርሻ የአርሶ አደሩን ምርት እና ምርታማነት ከመጨመር ባለፈ እንደ ሀገር ለሚደረገው የብልጽግና ጉዞ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑም ተገልጿል።
193 አርሶ አደሮች በማህበር በመደራጀት 102 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም እርሻ ጤፍ በዓመት 4 ጊዜ እያመረቱ እንደሆነ በጉብኝቱ ወቅት ተነግሯል።
የኦሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ፥ አርሷ አደሩ ምርታቸውን ወደ አቮካዶ እና ጤፍ እያስፋፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች ከዚህ በፊት ከጤፍ ምርት ያገኙት የነበረው ምርት በአሁኑ ጊዜ በእጥፍ እያገኙ እንደሆነ ተናግረዋል።
ባለፉት 3 ዓመታት 6 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ደረጃውን የጠበቀ የአቡካዶ ምርት መገኘቱን በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ሀብት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ተናግረዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ÷ የግብርና ስራ አሁን ያለበት ደረጃ በቀጣይ 5 ዓመታት የብልጽግና ጉዞን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ባለሃብት የሆኑ አርሶ አደሮች በወረዳው በአቮካዶ ምርት ላይ በመሰማራት ለውጪ ገበያ ማቅረብ ጀምረዋል ነው ያሉት፡፡
በጀሚላ ጀማል እና አዲሱ ሙሉነህ