አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት በደሴ ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ አደረገ፡፡
በዚህም ለተፈናቃይ ወገኖች ከ500 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የምግብ ድጋፍ መደረጉ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የአማራ ክልል የሃይማኖት ጉባኤ ሰብሳቢ መልዓከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም ቤተክርስቲያኗ ዘር፣ ቀለም እና ሃይማኖት ሳትለይ ድጋፍ ማድረጓን አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ከዚህ ቀደም መሰል ድጋፍ ማድረጉን ያወሱት መልዓከ ሰላም ኤፍሬም በመተከል፣ በደባርቅ እና በደሴ በአጠቃላይ ከ2 ሚሊየን 300 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል።
ድጋፉ ወደ ፊትም በአፋር ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረግ እንደሆነ እና ተፈናቃይ ወገኖችም እንዲበረቱ አባታዊ ምክራቸውን ማስተላለፋቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የድጋፍ ባለሙያ እና የተፈናቃዮች የድጋፍ አስተባባሪ አቶ ጌቴ ምህረቴ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ላደረገው ድጋፍ አመሥግነው ማኅበረሰቡም የተፈናቀሉ ወገኖችን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!