Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

መንግስት ለትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል- ዶክተር ሹመቴ ግዛው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ለትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምህርትን አገልግሎትና ጥራት ለማሻሻል የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ገለጹ።
በሀገራችን ጥራት ያለው ትምህርት እና ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲተገበሩ ለማድረግ የምርምር ዩንቨርሲቲዎች ከሌሎች የሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ልዩ በሚያደርጋቸዉ መልኩ ተለይተዉ በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
ከነዚህም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንጋፋዉና ስመ ጥሩ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንደሚገኝበትም ጠቅሰዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ባደረጉት ንግግር፥ በጥበበኞች ምድር በጋሞ አባቶችና ሽማግሌዎች በተቃኘችና በተያዘች በፍቅር ሰዎች ምድር ተገኝቸቼ በዚህ ታሪካዊ ቀን መልዕክት እንዳስተላልፍ እድል ስለተሰጠኝ ኩራት ይሰማኛል ብለዋል፡፡
ለዩንቨርስቲዉ 34ኛ ዙር ተመራቂ ተማሪዎች ለተጋባዥ እንግዶችና ለዩኒቨርስቲዉ ማህበረሰብ እንኳን ለዚች በጉጉት ለምትጠብቋት ቀን አደረሳችሁ ያሉት ዶክተር ሾመቴ፥ ትምህርትና እውቀት ድህነትን በማሸነፍ ዘላቂ ብልጽግናን ለማምጣት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
ትምህርት በጥሩ ሞራልና ሥነ ምግባር የተገነባ ማህበረሰብ ለማፍራት ያለውን የማይተካ ሚና በመረዳት፥ መንግሥት ከፍተኛ መዕዋለ ንዋይ በማፍሰስ የትምህርትና የስልጠና ዘርፉን በሰው ሃይል ልማት፣ በቁሳዊ አቅርቦቶችና በምቹ መዋቅራዊ አደረጃጀት እየደገፈ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ዘርፉ ከተንጋደደ ምንም ነገር ሊቃና እንደማይችል የራሳችን ሀገር የትምህርት ታሪክ ምስክር መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ሸመቴ ግዛው፥ ይህንንም በመገንዘብ ነው መንግስት ለትምህርትና ሥልጠና ልዩ ትኩረት የሰጠው ብለዋል።
በርካታዎቹ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በፍጥነት ወደ ድጅታል ሥነ ምህዳር እያደገና መጫወቻ ሜዳውም ከጊዜ ወደጊዜ እየተቀየረ ስለሆነ መጠነ ሰፊ የቴክኖሎጂ ልማትና ተጠቀሚነትን እንደሀገር ማረጋገጥ ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።
የምርምር ዩኒቨርሲቲዎችን ልዩ የሚያደርጋቸዉ ዋናዉ ጉዳይ በውስጣቸዉ የሚይዙት የልህቀት ማዕከላት መሆናቸውን ገልጸው፥ የልህቀት ማዕከላቱም እጅግ ዘመናዊ እና አለማቀፋዊ ደረጃ ያላቸዉ የምርምር ቤተ ሙከራዎች፥ ችግር-ፈቺ የሆኑ ምርምር ፕሮጀክቶች፤ ከማስተማር ይልቅ ወደምርምር የሚያዘነብሉ ተማሪዎችን፤ መምህራን እና ተመራማሪዎች ዋና ዋናዎቹ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ግብዓቶች መሆናቸውንም አብራርተዋል
የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 6 ሺህ 556 ተማሪዎች ዛሬ ያስመረቀ ሲሆን፥ ከተማሪዎቹ መካከልም 34 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።
በአመለወርቅ ደምሰው
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version