Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቅንልቦች የበጎ አድራጎት ማኅበር ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 29 ፣2014 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቅንልቦች የበጎ አድራጎት ማኅበር በአሸባሪው ትህነግ ወረራ ምክንያት ከዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ተፈናቅለው በባሕር ዳር ለተጠለሉ ወገኖች 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የምግብ ድጋፍ አድርጓል።
የቅንልቦች የበጎ አድራጎት ማኅበር ሰብሳቢ ዶክተር የውልሰው ካሴ፥ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ከሚኖሩ በጎ አሳቢ ግለሰቦች የሰበሰበውን የአይነት ድጋፍ በባሕር ዳር ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለተጠለሉ ተፈናቃይ ወገኖች ማስረከባቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ወይዘሮ ዘውዲቱ ገብረመድህን በአሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን ከዋግኽምራ መፈናቀላቸውን ነግረውናል።
8 ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ባሕርዳር መሸሻቸውን ነው የገለጹት፡፡ ወይዘሮ ዘውዲቱ በባሕር ዳር በተለያዩ በጎአድራጊ ግለሰቦች ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ለተደረገላቸው ድጋፍም አመስግነዋል።
አቶ ዓለሙ ፀሐዩ በበኩላቸው ታናሽ ወንድማቸው እና የእህታቸው ልጅ በወራሪው ቡድን ተገድለውባቸዋል፤ አራት ሴት ልጆቻቸው የት እንዳሉ እንደማያውቁ ነው የተናገሩት፡፡ በቅን አሳቢ ወገኖቻቸው በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
እርዳታውን የተቀበሉት የአማራ አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ጊዜያዊ የዕርዳታ አስተባባሪ ጀምበሩ ደሴ የተደረገው ድጋፍ ሌሎችም ለወገናቸው እንዲደርሱ የሚያነሳሳ ነው፤ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባልም ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version