አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና እና ግብርና ኮሌጅ በዛሬው እለት የድህረ ምረቃ እና ቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን አስመርቋል።
ኮሌጁ በዛሬ እለት በቢሾፍቱ ከተማ ያስተማረቀው በእንስሳት ህክምና እና በግብርና ኮሌጅ ያስተማራችውን ተማሪዎች ነው።
አንጋፋው ኬሌጅ 10 በዶክትሬት፤ 45 በማስተርስ ድግሪ፤ 38 በዲቪኤም እንዲሁም 59 በቪኤልቲ በአጠቃላይ 152 የድህረ ምረቃ እና ቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።
በምረቃ መርሃ ግብሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀናና የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፍቅሩ ረጋሳ ተገኝተዋል።
የእንስሳት ህክምና ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ሂካ ዋቅቶሌ እንዳሉት፤ ኮሌጁ ለሀገራችን ቀዳሚ የእንስሳት ህክምና ተቋም እንደመሆኑ መጠን በከፍተኛ ደረጃ በእንስሳት ህክምና ሙያ የሰለጠነ የሰው ሀይል በማፍራት እና የእንስሳት ጤናና የእንስሳት እርባታን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ኮሌጁ ሀገራዊ ተልኮውን ለመወጣትና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእድገትና ልዕቀት አቅጣጫን በመከተል የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን በማስፋፋት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
የእንስሳት ህክምና እና ግብርና ኮሌጁ ለሀገሪቱ ግንባር ቀደም የእንስሳት ህክምና ተቋም ሲሆን፤ ላለፉት 58 ዓመታት በተለያዩ ፕሮግራሞች ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል።
በቅድስት ተስፋዬ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!